የሰባት ዳኞች ሰበር ችሎት የፍርድ እና ውሳኔ አሰጣጥ ሥነ-ሥርዓት ላይ የቀረበ አጭር ምልከታ
በአልማው ወሌ ጠበቃና የህግ አማካሪ
1. መግቢያ፡ የችግሩ ታሪካዊ ዳራ እና የህግ ማዕቀፍ
1.1. ከ2013 ዓ.ም. በፊት የነበረው ያልተማከለ ሥርዓት፡ "የመግባቢያ ሰነድ" እና ውስንነቶቹ
አርስቱ ትኩረት ከተነፈጉት ሆኖም ግን ከመሰረታዊ የዳኝነት አካሄድ ጉዳዮች አንዱ ይመስለኛል፡፡ ከሰኔ 07 ቀን 1997 ዓ/ም ጀምሮ እስከ ጥር 2013 ዓ/ም ለነበሩት የስራ ጊዚያት የሰበር ችሎቱ አጠቃላይ ስልጣንና አሰራር በዋነኛነት ሲገዛ የነበረው በኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ህገ-መንግስት እና በፌዴራል ፍርድ ቤቶች አዋጅ ቁ. 25/1988 እንዲሁም በአዋጅ ቁጥር 454/1997 አግባብ ነበር። ባለሰባቱ ዳኞች ሰበር ችሎት በአዋጅ ቁጥር 454/97 አንቀፅ 2(4) ስር በተቀመጠው አግባብ ቀድሞ የተሰጠውን አስገዳጅ የህግ ትርጉም የመቀየር ስልጣን የነበረው ቢሆንም፣ ችሎቱ የሚመራበት ራሱን የቻለ ሥነ-ሥርዓት አልነበረውም። በእነዚህ ጊዚያት ጥቅም ላይ ሲውል የነበረው በተቋሙ ከ2001 ዓ/ም መጨረሻ የተዘጋጀውና ከ2002 ዓ/ም ጀምሮ ተግባራዊ የሆነው 'የመግባቢያ ሰነድ' ሲሆን፣ ሰነዱ በዋነኛነት የሚደነግገው አስገዳጅ ትርጉምን ለመቀየር የሚሰየሙት ዳኞች ቁጥር ቢያንስ ሰባት መሆን እንዳለበት እና ጉዳዩ በፕሬዝዳንቱ በኩል ለሰባት ዳኞች እንዲቀርብ የሚደረግበትን ሁኔታ ነበር። ሆኖም ሰነዱ የባለጉዳዮችን ሚና፣ የክርክር አመራርን እና የውሳኔ አገላለፅን በተመለከተ የሚገልጸው ነገር ያልነበረ ከመሆኑም በላይ የህግ ደረጃውም አወዛጋቢ ነበር። ሰነዱ አስራ ሶስት ያህል አስገዳጅ የህግ ትርጉሞች እንዲሻሻሉ በማስቻል አሰራሩ/ልምዱ በአዋጅ ቁጥር 1234/2013 ግልጽ የህግ ማዕቀፍ እንዲይዝ ከፍተኛ ሚና እንደተጫወተ የሚካድ አይመስለኝም፡፡
1.2 በአዋጅ ቁጥር 1234/2013 የመጣው ለውጥ፡ "ይታያል" ("to be heard") የሚለው ሐረግ አንድምታ
ከጥር 13 ቀን 2013 ዓ/ም ጀምሮ ስራ ላይ የዋለው የፌዴራል ፍ/ቤቶች አዋጅ ቁጥር 1234/2013 አንቀጽ 26 (1) እና (2) ቀድሞ የተሰጠዉን አስገዳጅ የህግ ትርጉም ለመለወጥ ጉዳዩ ከሰባት ያላነሱ ዳኞች በተሰየሙበት የሰበር ችሎት "እንዲታይ" እንደሚደረግ ይደነግጋል። ምንም እንኳን "ይታያል" የሚለው ቃል ምን ምን ሂደቶችን እንደሚያካትት በግልጽ የተቀመጠ ነገር ባይኖርም፣ የአዋጁ የእንግሊዝኛ ቅጂ ''....... the case to be heard....' የሚል ሀረግ ይዟል። በመሆኑም ሁለቱንም ቅጂዎች ተጣምረው ሲነበቡ፣ ሂደቱ የክርክር አቀራረብን፣ የዳኞችን ውይይት (Case Briefing) እና የውሳኔ አሰጣጥን ያካተተ ሙሉ የዳኝነት ሂደት መሆኑን መረዳት ይቻላል።
2. የክርክሩ የንድፈ-ሃሳብ መሰረት፡ የመሰማት መብት
2.1. 'መሰማት' እንደ መሰረታዊ መብት፡ ምንነት እና ወሰን
በፍትሕ ሥርዓቱ ከፍተኛው እርከን ላይ "መሰማት" የሚለው ሐረግ ከተራ የሥነ-ሥርዓት ጉዳይ እጅግ የላቀ ትርጉም ይይዛል። አንድ ወገን በሁሉም የታችኛው እርከን ፍርድ ቤቶች ላይ አስገዳጅ ትርጉም በሚሰጥ የሀገሪቱ የበላይ የዳኝነት አካል ፊት ክርክሩን እንዲያቀርብ የሚያስችለውን መሰረታዊ መብት ያመለክታል።
2.2. የህገ-መንግስታዊ ምሰሶዎች
ይህ መብት በህገ-መንግስታዊ መሰረቶች ውስጥ ጥልቅ ስር የሰደደ ሲሆን፣ ህጋዊ ታዓማኒነቱም ፍትሐዊ የሕግ ሥነ-ሥርዓት (Due Process) እና ወደ መጨረሻው የዳኝነት አካል የመቅረብ መብት (Access to the Court of Last Resort) ተብለው ከሚታወቁት ሁለት የህግ ምሰሶ መርሆዎች ይመነጫል። ፍትሐዊ የሕግ ሥነ-ሥርዓት "በመሰረታዊ ፍትሐዊነት" (fundamental fairness) ላይ ተመስርቶ ማንኛውም ሰው ጉዳዩን እንዲያቀርብ ፍትሐዊ እና ትርጉም ያለው ዕድል ሳያገኝ ህይወቱን፣ ነጻነቱን ወይም ንብረቱን እንዳይነፈግ የሚያረጋግጥ መሰረታዊ የህገ-መንግስታዊ ዋስትና ነው። ወደ መጨረሻው የዳኝነት አካል የመቅረብ መብት ደግሞ፣ ምንም እንኳን ፍጹም መብት ባይሆንም፣ ፍርድ ቤቱ አንዴ ጉዳዩን ለማየት ከፈቀደ ተከራካሪ ወገኖች ሙሉ የክርክር መብት እንዲኖራቸው የሚያስገድድ መርህ ነው።
2.3. የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ህግ አንድምታ
የመሰማት መብት ዓለም አቀፋዊ መገለጫ ያለው ሲሆን፣ ይህም ፈራሚ ሀገራትን በሚያስገድዱ ዓለም አቀፍ የህግ ሰነዶች ውስጥ በግልጽ ተካቷል። የዓለም አቀፍ የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች ቃል ኪዳን አንቀጽ 14 የተከራካሪ ወገኖችን የመሰማት መብት በግልጽ ይጠብቃል። የአፍሪካ የሰዎችና የህዝቦች መብቶች ቻርተር አንቀጽ 7(1)(ሀ) ደግሞ ተከራካሪ ወገኖች በግልጽ ችሎት የመሰማት መብት እንዳላቸው ያረጋግጣል። እነዚህ ዓለም አቀፍ ሰነዶች በኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ሕገ መንግሥት አንቀጽ 9(4) መሰረት የሀገሪቱ ህግ አካል በመሆናቸው በኢትዮጵያ ፍርድ ቤቶች ላይ ቀጥተኛ አስገዳጅነት አላቸው።
3. የችሎቱ ተጨባጭ አሰራር እና የሚፈጥረው የሥነ-ሥርዓት ክፍተት
3.1. በውይይት ወቅት የነበረው አሰራር እና የተደረጉ ማሻሻያዎች
ከጥር 13 ቀን 2013 ዓ/ም በፊት በተለይም ከ2011 ዓ/ም በፊት በተለወጡ ሰባት አስገዳጅ የህግ ትርጉሞች ላይ የሰባቱ ዳኞች ስም እና ፊርማቸው በፍርዱ ላይ ቢሰፍርም፣ በውይይቱ ጊዜ ሁሉም ዳኞች በአካል ተገኝተው ውይይቱ ሲከናወን እንዳልነበር ይታወቃል። የችሎቱ ውይይት በተሟላ የዳኞች ቁጥር መከናወን የጀመረው ከ2011 ዓ/ም ጀምሮ ሲሆን፣ ይህ አሰራር የሰበር ሥነ-ሥርዓት መመሪያ ከወጣበት ሚያዚያ 19 ቀን 2015 ዓ/ም በኋላም ተጠናክሮ ቀጥሏል።
3.2 የፍርድ እና ውሳኔ አነባበብ ሥነ-ሥርዓት፡ የልምድ እና የህግ ግጭት
3.2.1 ገራዊ የስነ ስርዐት ህግጋትና ልምዱ
የፍርድ መነበብን በተመለከተ የችሎቱ ወጥ ልምድ፣ ሁሉም ዳኞች በግልጽ ችሎት መሰየም ሳያስፈልግ በወቅቱ በተገኙት ጥቂት ዳኞች (በአብዛኛው ከአምስት በማይበልጡ) ብቻ ውሳኔው የሚከናወንበት ሂደት ነው። ይህ አሰራር ህጋዊ መሰረቱ ሲመረመር፣ የሰበር ሥነ-ሥርዓት መመሪያው ክፍተቱን ለመሙላት ወደ ሥነ-ሥርዓት ህጎች ይመራል። የፍትሐ ብሔር ሥነ-ሥርዓት ህግ አንቀጽ 181(3) "በዳኞች የተፈረመ ፍርድ፣ በሌሎች ዳኞች ሊነበብ ይችላል" በማለት በግልጽ ሲፈቅድ፣ የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ-ሥርዓት ህግ አንቀጽ 149(1) ግን "ውሳኔው በሚያነበው ዳኛ መፈረም አለበት" በማለት ጥብቅ የሆነ አሰራርን ያስቀምጣል። ይህ በሁለቱ ህጎች መካከል ያለው ልዩነት፣ በተለይ እንደ አስገዳጅ ትርጉም መለወጥ ባለ ታሪካዊ ክስተት ላይ የትኛው መርህ የበላይነት ሊኖረው እንደሚገባ ጥልቅ ትንታኔ የሚያስፈልገው ነው። የፍትሐ ብሔር ሥነ-ሥርዓት ህጉ ድንጋጌ የሰበር ሰሚ ችሎቱ አሰራር ህጋዊ ሽፋን ያለው እንዲመስል ያደርጋል። ይህ ግን የችግሩን ምንጭ ከማያገናዝብ ጠባብ የህግ ወግ አጥባቂነት (Legal Formalism) የሚመነጭ እይታ ነው። የሰባት ዳኞች ችሎት አስገዳጅ የህግ ትርጉምን የሚሽርበት ሂደት ከተራ የዳኝነት ተግባር እጅግ የላቀና ከፊል-ህግ አውጪነት (quasi-legislative) ባህሪ ያለው በመሆኑ፣ በተራ የሥነ-ሥርዓት ህግ ብቻ ሊመራ አይገባም። አንድ አስገዳጅ ትርጉም ሲሻር፣ የችሎቱ ሙሉ ስብጥር በግልጽ ችሎት በአካል ተገኝቶ ውሳኔውን ማሳወቁ፣ ለውሳኔው የሚሰጠውን የከበሬታ ደረጃ (solemnity) እና የህዝብ አመኔታ ያጎለብታል። የዳኞቹ የጋራ ገጽታ፣ ውሳኔው በዘፈቀደ ሳይሆን በከፍተኛ ጥንቃቄና በጋራ ተቋማዊ ኃላፊነት የተወሰነ መሆኑን ለህግ ማኅበረሰቡና ለመላው ህዝብ የሚያሳይ ኃይለኛ ምሳሌያዊ ማረጋገጫ ነው። የፍትሐዊ የፍርድ ሂደት መብት፣ የክርክር አቀራረብን ብቻ ሳይሆን የፍርድ ቤቱ ውሳኔ ለህዝብ ይፋ እስከሚሆንበት ጊዜ ድረስ ያለውን ሂደት የሚሸፍን ነው። በመሆኑም የውሳኔው በይፋ መነበብ፣ ፍትሕ መፈጸም ብቻ ሳይሆን ሲፈጸምም መታየት አለበት የሚለውን መርህ የሚያረጋግጥ ወሳኝ የሥነ-ሥርዓት ክፍል ነው። አሁን ያለው አሰራር ግን፣ ምንም እንኳን በፍትሐ ብሔር ሥነ-ሥርዓት ህግ ስር መደበቂያ ቢኖረውም፣ ይህንን ወሳኝ መርህ ይጥሳል።
3.2.2 የህገ-መንግስቱ እና የዓለም አቀፍ ሰነዶች
ከሁሉም በላይ ይህ የሥነ-ሥርዓት ጉዳይ መታየት ያለበት ከፍ ሲል በህገ-መንግስቱ እና ኢትዮጵያ ባጸደቀቻቸው ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ሰነዶች አንጻር ነው። የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ህገ-መንግስት በአንቀጽ 20(1) ማንኛውም ሰው "በግልጽ ችሎት" የመዳኘት መብት እንዳለው ይደነግጋል። በተጨማሪም የዓለም አቀፍ የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች ቃል ኪዳን ማንኛውም የፍርድ ውሳኔ "ለህዝብ ይፋ መሆን አለበት" በማለት ያስገድዳል። የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ መብቶች ኮሚቴም "ለህዝብ ይፋ መሆን" የሚለው ሐረግ ዋነኛ ትርጉሙ ውሳኔው በግልጽ ችሎት መነበብ መሆኑን አስቀምጧል።
4. ማጠቃለያ እና የውሳኔ ሃሳብ
ምንም እንኳን በሰበር ሰሚ ችሎት አሰራር ላይ በርካታ ማሻሻያዎች ቢደረጉም፣ የባለሰባት ዳኞች ችሎት የውሳኔ አነባበብ ልምድ፣ በጠባብ የህግ ትርጓሜ ህጋዊ ሊመስል ቢችልም ከችሎቱ ሚና እና ከሚጠበቀው የተቋማዊ ግልጽነትና የህዝብ ተጠያቂነት መርሆዎች ጋር ያልተጣጣመ ነው። ይህ አሰራር፣ በተለይ አስገዳጅ የህግ ትርጉም በሚለወጥበት ወቅት፣ ሂደቱ የሚጠይቀውን ክብደት የሚመጥን ከባድ የሥነ-ሥርዓት ክፍተት ይፈጥራል። ስለሆነም ችሎቱ ውሳኔውን በተሟላ እና በግልጽ ችሎት የማንበብ ልምድን ተግባራዊ ማድረግ ይኖርበታል። አሁን ስራ ላይ ያለው የሰበር ሥነ-ሥርዓት መመሪያም፣ ይህንን አሰራር አስገዳጅ የሚያደርግ ግልጽ ድንጋጌ እንዲይዝ ሊደረግ ይገባል።
ϖ እርስዎስ ጉዳዩ ትልቅ ችግር ተደርጎ ሊወሰድ አይገባም ይላሉ?፣ ችግር ነው ካሉስ በምን ምክንያቶች? መፍትሔውስ ምን መሆን አለበት ይላሉ?
The content of this article is intended to provide a general guide to the subject matter. Specialist advice should be sought about your specific circumstances.