ARTICLE
3 March 2026

የወረቀት ላይ አጋር፦ የሰበር መመሪያው አንቀጽ 13 እና የፍርድ ቤት አጋር (Amicus Curiae) የተግባር ክፍተት

5A Law Firm LLP

Contributor

5A Law Firm LLP is Ethiopia's only law firm founded entirely by former judges, with 114+ years of combined judicial and legal experience. Based in Addis Ababa — Africa's diplomatic capital — we advise foreign investors, multinationals, and international organizations on investment law, corporate transactions, tax, arbitration, and regulatory compliance.
የፌ/ጠ/ፍ/ቤት ሰበር ችሎት በፌ/ፍ/ቤቶች አዋጅ ቁጥር 1234/2013 አንቀጽ 10 እና አንቀጽ 2(4) መሠረት "መሠረታዊ የሕግ ስህተት" (Fundamental Error of Law) ባለባቸው ጉዳዮች ላይ የመ
Ethiopia Litigation, Mediation & Arbitration

1. መግቢያ

የፌ/ጠ/ፍ/ቤት ሰበር ችሎት በፌ/ፍ/ቤቶች አዋጅ ቁጥር 1234/2013 አንቀጽ 10 እና አንቀጽ 2(4) መሠረት "መሠረታዊ የሕግ ስህተት" (Fundamental Error of Law) ባለባቸው ጉዳዮች ላይ የመጨረሻ ውሳኔ የመስጠት ስልጣን ያለው ከመሆኑም በላይ የህግ ትርጉም የያዙ ውሳኔዎቹ በየትኛው እርከን በሚገኙ የበታች ፍርድ ቤቶች ላይ የአስገዳጅነት (Interpretative Binding Precedent) ሃይል አላቸው። ይህን ከባድ ኃላፊነት ለመወጣት ፌ/ጠ/ፍ/ቤቱ የራሱን የውስጥ አሠራር ለማዘመን የሰበር ሥነ-ሥርዓት መመሪያ ቁጥር 17/2015'ን' አውጥቶ ከሚያዚያ 19 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ አድርጓል።

የዚህ መመሪያ አንቀጽ 13 ለኢትዮጵያ የዳኝነት ሥርዓት አዲስ የሆነውን "የፍርድ ቤት አጋር" (Amicus Curiae) አሠራርን ያስተዋውቃል። ከዚህ መመሪያ በፊት በ2013 ዓ/ም የምርጫ ጉዳይ ላይ የህገ መንግስት አጣሪ ጉባዔ ተግባራዊ ያደረገው የባለሙያዎች መስማት የቅርብ ጊዜ ትውስታችን ሲሆን የፌዴሬሽን ምክር ቤትን ስልጣንና ተግባር ለመዘርዘር የወጣ አዋጅ ቁጥር 1261/2013 አንቀፅ 15 (4) ስር የባለሙያ አስተያየት ሊቀርብ የሚችልበትን አግባብ ያስቀመጠ ሲሆን የህገ መንግስት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ የአሰራር ስነ ስርዓት ደንብ ቁጥር 7/2017 አንቀፅ 2(17) ስር የጉባዔ አጋዥ(የአሚከስ ኩሪ አቅራቢ) ትርጉም ሰጥቶ ስርዓቱ ጥቅም ላይ ሊውል የሚችልበትን አግባብ ደንግጎ ይገኛል፡፡ ሰበር ችሎቱን በሚመለከት አዋጅ ቁጥር 1234/2013 እንደ አዋጅ ቁጥር 1261/2013 ስለአጋር ባለሙያ በግልፅ ያስቀመጠው ድንጋጌ ሳይኖር በሰበር ስነ ስርዓቱ መመሪያ ላይ ተደንግጎ የምናገኛው ቢሆንም በእኔ ልምድና መረጃ መሰረት መመሪያው ከወጣ በኋላ ባሉት ጊዜያት ይህ አሠራር መሬት ሲነካ አልታየም። ይህ ጽሑፍ የዚህን አንቀጽ ህጋዊነት አስፈላጊነት እና የተግባራዊነት ተግዳሮቶች በአጭሩ ለመተንተን የተሞከረበት ነው፡፡

2. የሕጋዊነት ጥያቄ፡- መመሪያው ከአዋጁ ሥልጣን በላይ ነውን? (The Ultra Vires Issue)

የመጀመሪያው እና መሠረታዊው የሕግ ክርክር የሚነሳው የመመሪያው አንቀፅ ሕጋዊ ምንጭ ላይ ነው። መመሪያ ቁጥር 17/2015 የወጣው በአዋጅ ቁጥር 1234/2013 አንቀጽ 27(1) እና 55 (2) ድንጋጌዎች መሠረት ሲሆን የአንቀፅ 27(1) ድንጋጌ "የሰበር አቤቱታ የሰበር ችሎት እንዲያየው የሚቀርብ ማመልከቻ... የተጠየቀውን ዳኝነት እና ''በጠቅላይ ፍርድ ቤት በሚወጣው መመሪያ መሰረት ተዘጋጅቶ መቅረብ አለበት።" የሚል ይዘት አለው፡፡ ይህ የአዋጁ ድንጋጌ ለጠቅላይ ፍርድ ቤት የሰጠው ስልጣን "የአቤቱታ አቀራረብን" (Application Procedure) የሚመለከት ዝርዝር መመሪያ እንዲያወጣ እንጂ በክርክር ሥነ-ሥርዓት ውስጥ አዲስ ተዋንያን (New Procedural Actor) ወይም "የፍርድ ቤት አጋር" የሚባል አዲስ አካል እንዲፈጥር ግልጽ ሥልጣን አይሰጥም። መመሪያው የሰበር ችሎት ስነ ስርዓት ስለመሆኑ በመመሪያው አንቀፅ አንድ ስር ከመቀመጡም በላይ ሙሉ ድንጋጌዎቹና ይዘታቸ የሰበር ክርክር አመራር ስርዓትን የሚገዙ መሆናቸው እየታወቀና አንቀፅ 13 ዝርዝር ይዘቱም ስለሰበር ችሎት አጋር የሚደነግግ ሁኖ እያለ የመመሪያው አንቀፅ አርዕስቱ የሰበር ችሎት አጋር የሚለውን ሀረግ ከመጠቀም ተቆጥቦ ለምን ለሁሉም ፍርድ ቤቶች ተግባራዊ ሊሆን እንደሚችል ቃል 'የፍርድ ቤት አጋር' የሚል ሀረግ እንደተመረጠ የድንጋጌውን አቀራረፅ ችግር የሚያሳይ ነው ከሚባል በስተቀር ከመመሪያው አንቀፅ 2(2) ስር ስለፍርድቤት ከተሰጠው ትርጉምና ከራሱ ከአንቀፅ 13 ሙሉ ይዘት ጋር የማይጣጣም ሁኖ ይታያል፡፡

በሕግ አተረጓጎም መርህ (Statutory Interpretation) ሥነ-ሥርዓታዊ መብቶችን ወይም አዳዲስ የክርክር አካላትን ማስተዋወቅ የሕግ አውጪው (Legislature) ድርሻ እንጂ በፍርድ ቤት የአሠራር መመሪያ (Administrative Directive) የሚሸፈን አይደለም። የፍርድ ቤት አጋርን ማሳተፍ የክርክሩን ባህሪ፣ ጊዜ እና ወጪ የሚቀይር በመሆኑ ይህ ጉዳይ በአዋጁ ውስጥ በግልጽ ሊቀመጥ ይገባ ነበር።

እንዲሁም አዋጅ ቁጥር 1234/2013 አንቀጽ 17(2)(መ) ድንጋጌ ሲታይም የፌ/ጠ/ፍ/ ቤት ፕሬዚዳንት "በዚህ አዋጅ ላይ በተጠቀሰው መሠረት በፌ/ጠ/ፍ/ቤት መውጣት ያለባቸው ደንቦች እና መመሪያዎች እንዲዘጋጁና እንዲወጡ በማድረግ ተግባራዊ መሆናቸውን ያረጋግጣል" የሚል ሥልጣን ቢሰጥም ይህ ግን ያሉትን የሕግ ማዕቀፎች ተግባራዊ የሚያደርጉ መመሪያዎችን ለማውጣት እንጂ ሙሉ በሙሉ አዲስ የሥርዓት አሠራርን ለማስተዋወቅ አይደለም። በመሆኑም፣ መመሪያው ቀጥተኛ የአዋጁ ድንጋጌ ሳይኖር ጉልህ የሆነ የሥርዓት ፈጠራን ያስተዋወቀ ይመስላል። ስለሆነም በአዋጁ ውስጥ ስለ "ፍርድ ቤት አጋር" ምንም ሳይጠቀስ በመመሪያ ደረጃ ብቻ መደንገጉ መመሪያው ከወላጅ ሕጉ ሥልጣን ውጪ ወጥቷል (Ultra Vires) የሚል የሕግ ክርክር ያስነሳል። ስለሆነም የድንጋጌው ምንጭ ህጋዊ መሰረቱና የቃላት አጠቃቀሙና ሙሉ ይዘቱ የማይጣጣሙ መሆናቸው በመመሪያው ህጋዊነት እና አቀራርፅ ላይ ሊነሱ የሚችሉ ጥያቄዎች ናቸው፡፡

3. የሰበር ዓላማ እና የ"ፍርድ ቤት አጋር" አስፈላጊነት (The Doctrinal Nexus)

ምንም እንኳን የሕጋዊነት ጥያቄ ቢኖርም በፅንሰ-ሀሳብ ደረጃ (Doctrinally) የፍርድ ቤት አጋር ለሰበር ችሎት እጅግ አስፈላጊ መሆኑ ይታመናል፡፡ እንደሚታወቀው የሰበር ችሎት የሚሰጣቸው በርካታ ውሳኔዎች ለተከራካሪ ወገኖች ብቻ ሳይሆኑ ለመላው የሀገሪቱ ፍርድ ቤቶች ገዥነት ያላቸው፤ እንደ ሕግ ሁነው የሚያገለግሉ ናቸው፡፡ ስለሆነም ችሎቱ አንድን የሕግ ነጥብ ሲተረጉም ትርጓሜው በኢኮኖሚ፣ በማህበራዊ ጉዳዮች ወይም በሰብዓዊ መብቶች ላይ የሚያመጣውን ሰፊ ተፅእኖና አንድምታ (Wider impact and implication) መረዳት እጅጉን ጠቃሚ እና የሰበር ዳኝነት አካሄዱ የግድ የሚለው ጉዳይ ነው፡፡ በሰበር ስነ ስርዓት መመሪያው አንቀጽ 13(1) ስር እንደተቀመጠው የፍርድ ቤት አጋር "ሳይንሳዊ እና ሙያዊ ትንታኔ" ይሰጣል። ይህ ድንጋጌ መነሻው ዳኞች የሕግ ባለሙያዎች ቢሆኑም ውስብስብ በሆኑ እንደ ባንክ፣ ኢንሹራንስ፣ ህክምና ወይም ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ላይ የዘርፉን ጥልቅ እውቀትና ልምድ ላይኖራቸው ይችላል የሚለው አመክንዮ ስለመሆኑ ይገመታል፡፡ ሆኖም ድንጋጌው የፍርድ ቤት አጋርን ሚና ሲገልጽ "በቀረበው ጉዳይ ላይ ምንም ዓይነት ጥቅም የሌለው" ይላል። ይህ ትክክል ነው ሊባል የሚችል ቢሆንም አሠራሩን ከሰበር ችሎቱ "መሠረታዊ የሕግ ስህተት" የማረም ሥልጣን ጋር ማጣጣም ግን አስፈላጊ ነው፡፡ የፍርድ ቤት አጋር ማቅረብ ያለበት የሕግ ትንተና እንጂ የጭብጥ (Fact) ትንተና መሆን የለበትም። ምንም እንኳን ጭብጥ የሚለው ቃል ከአዋጅ ቁጥር 2 (4)፣ 10 ፣ 27 እና 28 (3) ድንጋጌዎች መንፈስና ይዘት ሲታይ የህግ እንጂ የፍሬ ነገር ነጥብ ሊሆን እንደማይችል ግንዛቤ የሚያዝበት ጉዳይ ነው የሚል ክርክር ሊቀርብ የሚችል ቢሆን የችሎቱ አጋር በዚህ ረገድ ሊኖረው ከሚችለው የግንዛቤ ደረጃና በአጋሩ ሊቀርብ የሚችለው አስተያየት ወይም ምክረ ሀሳብ ከመሆኑ አኳያ፣ እንዲሁም መመሪያው የሚያስፈልገው የአዋጁ ድንጋጌዎችን ለማስፈፀም የሚያስችሉ ዝርዝር ድንጋጌዎችን ይዞ መገኘት ከመሆኑ ጋር ተዳምሮ ሲታይ መመሪያው ይህንን በግልጽ አለመለየቱ በተግባር ላይ ግራ መጋባት ሊፈጥር ይችላል።

4. የተግባራዊነት ችግር፡- ለምን በተግባር ሊውል ያልቻለ ድንጋጌ ሆነ?

የሰበር መመሪያው ከወጣ ሶስት አመታት ሊሞሉት ጥቂት ወራት የቀሩት ቢሆንም ተጠቃሹ ድንጋጌ በሥራ ላይ ሲውል አልታየም። በዚህ ረገድ በምክንያትነት ሊቀርቡ የሚችሉት ምክንያቶች የሚከተሉት ይመስሉኛል፡፡ ከእነዚህም አንዱ ምክንያት የሰበር የዳኝነት ስርዓት ባህል (Cassation System Conservatism) ነው፡፡ እንደሚታወቀው የፌ/ጠ/ፍ/ቤት የሰበር ስርዓት እጅግ ጠባብ በሆኑ ምክንያቶች ብቻ የበታች ፍርድ ቤቶች የሰጧቸውን የመጨረሻ ውሳኔዎች የሚታረሙበት ሁኖ የማስረጃ ጉዳይ ሙሉ በሙሉ የማይቀርብበት ስርአት ነው፡፡ በተለመደው የይግባኝ ወይም የስር ፍርድ ቤት ክርክር ሂደቱ "Adversarial" (የተከራካሪዎች ፍልሚያ) የሚባለው ስርዓት ጎልቶ ይታያል፤ ይኸውም ዳኛው በተከራካሪዎች በሚቀርብ ማስረጃ እና ክርክር ላይ ተመስርቶ እውነትን ይፈልጋል፡፡ ሆኖም ከላይ እንደተጠቀሰው ወደ ፌ/ጠ/ፍ/ቤት ሰበር ችሎት ስንመጣ ሁኔታው የተለየ ይሆናል፡፡ የሰበር ችሎት ሥልጣን የተገደበው "መሠረታዊ የሕግ ስህተት" (Fundamental Error of Law) በማረም ላይ ብቻ ነው። በመሆኑም የፍሬ ነገር ክርክሮች ወይም የማስረጃ ምዘና ጥያቄዎች ለሰበር ችሎት አይቀርቡም። ይህ የሚያሳየው የሰበር ስርዓታችን ዋና ትኩረት በተከራካሪዎች የግል መብት (Private Rights) ላይ ብቻ ሳይሆን የሕግን ትክክለኛ አተረጓጎም እና የፍርድ ቤቱን የሕግ የበላይነት የማረጋገጥ ሥልጣን (Public Function of the Court) ላይ መሆኑን ነው። በዚህም ምክንያት በሰበር ደረጃ የተከራካሪ ወገኖች ሚና እንደ ታችኛው ፍርድ ቤቶች ሰፊ አይደለም። ተከራካሪዎች በበታች ፍርድ ቤቶች የመሰማት መብታቸውን በበቂ ሁኔታ የተጠቀሙ በመሆናቸው በሰበር ደረጃ ፍርድ ቤቱ የሕግ ስህተቱን ለማረም የግድ የተከራካሪዎችን የቃል ክርክር በስፋትና በፍሬ ነገር ላይ አያስተናግድም። ይህ "በሕግ እና በአዋጅና በመመሪያው አግባብ ተዘጋጅቶ በቀረበ የሰበር አቤቱታ ይዘት ላይ ያተኮረ" (Document-based and Law-centric) የሰበር ባህርይ ለ"ፍርድ ቤት አጋር" (Amicus Curiae) አሠራር ምቹ ሁኔታን የሚፈጥር ነው ተብሎ ሊወሰድ የሚችል ነው፡፡ ምክንያቱም የፍርድ ቤት አጋር አስተያየት ወይም ምክረ ሃሳብ የሚያስፍልገው ለግለሰቦች ጥቅም ለመከራከር ወይም ማስረጃ ለመመዘን ሳይሆን ለሰበር ችሎቱ ውስብስብና ረቂቅ የሆነ የሕግ ትንተና በሚገባ ተረድቶ ጥራት ያለውን የህግ ትርጉም ለመስጠት እንዲችል ነው፡፡ ስለሆነም የሰበር ችሎቱ ከተከራካሪዎች "የማሸነፍ ፍላጎት" ይልቅ በሕግ ጥራት ላይ የሚያተኩር ከሆነ ከባለጉዳዮች ተፅእኖ የጸዳ የሙያዊ አጋር (Amicus) አስተያየት መቀበል ለችሎቱ ዓላማ (Mission) ይበልጥ ተስማሚ ነው። ከዚህ አንፃር ሲታይ ችግሩ አጠቃላይ የክርክር ስርዓታችን ሂደት "Adversarial" መሆን ሳይሆን የሰበርን ዓላማ (የሕግ እርማት) ከግለሰቦች ክርክር (Dispute Resolution) ነጥሎ ያለማየት ልማድ ነው። የሰበር ችሎቱ በሕግ ትርጓሜ ላይ የሚያተኩር እንደመሆኑ የተከራካሪዎችን ተሳትፎ ገድቦ የባለሙያዎችን (Amicus) ተሳትፎ ማበረታታት ከሰበር ፍልስፍና ጋር የሚጣጣም እንጂ የሚጋጭ ስላልሆነ የሰበር ችሎቱ ልዩ ባህርይና የተከራካሪዎች ሚና ሳይደበላለቁ እና የፍሬ ነገር ጉዳይ ሁልጊዜ ተመሳሳይ ማጣራትን እንደማይጠይቅ ግንዛቤ በመያዝ ስርዓቱን ተግባራዊ ማድረግ ተገቢነት ይኖረዋል፡፡

ሁለተኛው ምክንያት በተጠቃሹ የመመሪያው ድንጋጌ ንዑስ አንቀፅ ሁለት ስር "የሰበር ችሎቱ... አጋሮችን መስማት ተገቢ መሆኑን ካመነ... ሊቀበል ይችላል የሚለው አገላለፅ የአነሳሽነት ጉዳይን የመገደቡ ሁኔታ ይመስለኛል፡፡ ይህ ንዑስ ድንጋጌ የሚያሳየው ኃላፊነቱ ሙሉ በሙሉ በችሎቱ ላይ መውደቁን ነው። ችሎቱ ካልጠራ በስተቀር የሙያ ማህበራት ወይም ባለሙያዎች "የፍርድ ቤት አጋር መሆን እንፈልጋለን" ብለው ማመልከት የሚችሉበት ዕድል በመመሪያው አልተመቻቸም። በሌሎች ሀገራት (ለምሳሌ በደቡብ አፍሪካ ወይም ብራዚል) ፍላጎት ያላቸው አካላት ለፍርድ ቤቱ በማመልከት (Motion for leave to file amicus brief) መሳተፍ እንደሚችሉ አግባብነት ያላቸው ሰነዶች ያሳያሉ፡፡ በእና አገርም አዋጅ ቁጥር 1261/2013 አንቀፅ 15(4) እና በህገ መንግስት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ የአሰራር ሰነ ስርዓት አንቀፅ 2(16) አግባብ በምክር ቤቱ ወይም በጉባዔው አነሳሽነት ብቻ ሳይሆን በራሱ በአጋሩ ተነሳሽነት ጥያቄው የሚቀርብበት አግባብ መኖሩን የሚያሳዩ የህግ ማዕቀፎች አሉን፡፡ ከሰበር ስርዓት መሰረታዊ ዓላማ አንፃር በእነዚህ ህግጋት ስለአጋሩ የተመለከቱት አግባቦች ጥሩ ተሞክሮ ተደርገው ቢወሰዱ ችግር ያለው ሁኖ አይታይም፡፡ የሰበር ችሎት ስነ ስርዓት መመሪያ ግን ይህንን በር የዘጋ በመሆኑ ዳኞች በራሳቸው ተነሳሽነት እስካልጠሩ ድረስ አንቀጹ ተግባራዊ ሊሆን አልቻለም። ሶስተኛውና የመጨረሻው ምክንያት ተደርጎ ሊነሳ የሚችለው የአሰራር ስርዓትን የዘረጋ ዝርዝር ሰነድ/ ደንብ ያለመኖሩ ነው፡፡ ተጠቃሹ መመሪያ አጋሩ "እንዴት እንደሚመረጥ" "የጥቅም ግጭት (Conflict of interest) እንዴት እንደሚጣራ" እና "ወጪውን ማን እንደሚሸፍን" አይገልጽም። በዚህ ረገድ የስርዓትና አሰራር ግልጽነት ያለመኖር ዳኞች አሠራሩን ከመተግበር እንዲቆጠቡ ያደርጋቸው መስሎኝ ይታየኛል፡፡

5. ማጠቃለያ እና ምክረ-ሀሳብ

የሰበር ሥነ-ሥርዓት መመሪያው አንቀጽ 13 የፍርድ ቤት አጋርን ማካተቱ ለሰበርና አስገዳጅ የህግ ትርጉም ስርዓት ዕድገት ወሳኝ እርምጃ ተደርጎ ሊወሰድ የሚችል ነው። በተለይም የሰበር ችሎቱ የህግ ትርጉም ያለባቸው ውሳኔዎች አስገዳጅ በሆኑበት የዳኝነት ስርዓት የሕግ ትርጓሜው ጥራት (Quality of Reasoning) እንዲጨምር ያግዛል ተብሎ ይታመናል፡፡ ሆኖም አሁን ባለው ሁኔታ አንቀጹ " በሀሳብ ተፀንሶ፣ በወረቀት ከተወለደ በኋላ ህይወት ሳይኖረው የሚኖር ህግ" ሁኖ የቀረ ይመስለኛል፡፡ ይህንን ለመቅረፍ የሚቻለው አንዱ መንገድ አዋጁን በማሻሻል ነው፡፡ የፍርድ ቤት አጋር ጉዳይ የመብት እና የሥነ-ሥርዓት ጉዳይ በመሆኑ በሚቀጥለው የፍርድ ቤቶች አዋጅ ማሻሻያ ላይ በግልጽ ሊካተት ይገባል። ይህም የ"Ultra Vires" ክርክርን ያስወግዳል። ሌላው አስተያየቱን ወይም ምክሩ ለማቅረብ አነሳሹ ችሎቱ ብቻ እንዳይሆን በማድረግ የማመልከት መብቱን ለአጋሮቹም የሚሰጥ ስርዓት መዘርጋት መቻል ነው፡፡ ይህም መመሪያውን በማሻሻል ወይም በልምድ (Practice Direction) ባለሙያዎች እና ተቋማት በራሳቸው ተነሳሽነት የፍርድ ቤት አጋር ለመሆን የሚያመለክቱበት ስርዓት መፍቀድን ሊያካትት ይችላል፡፡ እንዲሁም አሰራሩ የሰበር ችሎቱን የዳኝነት ስራ ጥራት የሚጨምር ስለመሆኑ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኮች ለሰበር ችሎት ዳኞች ሊዘጋጁና ድንጋጌው በተግባር ላይ እንዲውል ማስቻል የግድ ይላል፡፡ እስካሁን ድንጋጌው ስራ ላይ ያልዋለው የህጉ እድሜ አጭር ሁኖ ወይም ሙያዊ አስተያየት ወይም ምክረ ሃሳብ የሚያስፈልገው የህግ ጭብጥ ሰበር ችሎቱ ሳያጋጥመው ቀርቶ ነው የሚል አጠቃላይ ግምት መኖሩን መረጃዎች ቢያሳዩም ሳይንሳዊ ጥናት አደርጎ ጉዳዩን መለየቱ እንደተጠበቀ ሁኖ በመመሪያው ላይ ተጠቃሹ ድንጋጌ የገባው ዝም ተብሎ ወይም በግምት ወደፊት ሊከሰት ችግሩ ሊኖር ሊያጋጥም ይችላል በሚል ድምዳሜ እንዳልሆነ ይታሰባል፡፡ ስለሆነም ከህገ አወጣጥ መሰረተ ሃሳብ አንፃር ሲታይም አንድ ሕግ "ከጥቅም ውጪ ሆኗል" (Disused) የሚባለው፣ ሕጉ በይፋ ሳይሻር (De jure valid) ነገር ግን በተለያዩ ምክንያቶች ለረጅም ጊዜ በተግባር ሳይውል (Non-enforcement) ሲቀር ነው። ይህንን ፅንሰ-ሀሳብ ይዘን ጉዳዩን ስንመለከተውም ስለ "ፍርድ ቤት አጋር" የሚደነግገው የሰበር ስነ ስርዓት መምሪያ ቁጥር 17/2015 አንቀፅ 13 መመሪያው ከጸደቀ ከሁለት ዓመት ተኩል በላይ ቢሆነውም አንዴም ተግባራዊ ሲደረግ አለመታየቱ ሕጉ ህልውና ቢኖረውም ውጤታማነቱን ያጣ "ያንቀላፋ ሕግ"(Dormant Law) ወደ መሆን እየተሸጋገረ መሆኑን ያሳያል።

6. ድምዳሜ

የፍርድ ቤት አጋር (Amicus Curiae) በፌ/ጠ/ፍ/ቤት ሰበር ችሎት መኖር አግባብነት የሌለውና አስፈላጊ አይደለም ሊባል የማይችል ነው፡፡ ስርዓቱ የሕግ ትርጓሜን ጥራት እና ተቀባይነት ለማረጋገጥ ወሳኝ መሳሪያ ነው። ነገር ግን ይህንን አሠራር ያለ በቂ የሕግ ማዕቀፍ እና የተግባር ዝግጁነት በመመሪያ ብቻ ማስቀመጥ የምናየውን የአፈጻጸም ክፍተት ፈጥሯል። ስለሆነም ጥልቅ የሆነ ጥናት ተደርጎና በዚህ ረገድ የዳበረ ልምድ ያላቸው የዳኝነት ስርዓቶች ከአገራችን ተጨባጭ ሁኔታዎች ጋር ታይተውና ተዛምደው ስርዓቱ ህይወት እንዲኖረው ማድረግ ተገቢ ነው የሚል እምነት አለኝ፡፡ እርስዎስ ምን ይላሉ??

The content of this article is intended to provide a general guide to the subject matter. Specialist advice should be sought about your specific circumstances.

[View Source]

Mondaq uses cookies on this website. By using our website you agree to our use of cookies as set out in our Privacy Policy.

Learn More