ARTICLE
3 March 2026

ሰበር አጣሪ ችሎት፦ የባለ5ቱ ዳኞች ሰበር ችሎት "በር ጠባቂው" ችሎት

5A Law Firm LLP

Contributor

5A Law Firm LLP is Ethiopia's only law firm founded entirely by former judges, with 114+ years of combined judicial and legal experience. Based in Addis Ababa — Africa's diplomatic capital — we advise foreign investors, multinationals, and international organizations on investment law, corporate transactions, tax, arbitration, and regulatory compliance.
የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ሕገ መንግስት ለፌ.ጠ.ፍ.ሰ.ች በሀገሪቱ የዳኝነት ሥርዓት መዋቅር ውስጥ ልዩ እና ወሳኝ ቦታ ማስያዙ ይታወቃል። በሕገ-መንግሥቱ የተቋǔ
Ethiopia Litigation, Mediation & Arbitration

ሰበር አጣሪ ችሎት፦የባለ5ቱ ዳኞች ሰበር ችሎት "በር ጠባቂው" ችሎት

የፌ/ ጠ/ፍ/ቤት ሰበር አጣሪ ችሎት የሰበር አቤቱታን በቃል የሚሰማበት ሂደት ሕጉና አሠራሩ

1.1. የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ሕገ መንግስት ለፌ.ጠ.ፍ.ሰ.ች በሀገሪቱ የዳኝነት ሥርዓት መዋቅር ውስጥ ልዩ እና ወሳኝ ቦታ ማስያዙ ይታወቃል። በሕገ-መንግሥቱ የተቋቋመው የዚህ ችሎት ዋነኛ ሥልጣን እንደ ሦስተኛ ደረጃ የይግባኝ ሰሚ ችሎት ሆኖ ማንኛውንም ስህተት ማረም ሳይሆን ከሥር ፍርድ ቤቶች በተሰጡ የመጨረሻ ውሳኔዎች ላይ የተፈጸሙ "መሠረታዊ የሕግ ስህተቶችን" ማረም ነው። ይህ ሥልጣን በመላ ሀገሪቱ ወጥ የሆነ የሕግ ትርጉምና አተገባበር እንዲሰፍን ለማድረግ ቁልፍ ሚና ይጫወታል። የሰበር ችሎቱ መሰረታዊ የሆኑ የህግ ስህተት ያለባቸውን የመጨረሻ ውሳኔዎችን ለማረም የሚያስችለውን ህገ መንግስታዊ ስልጣኑን ዝርዝር ስርዓት በተመለከተ በዝርዝር ህግ ሊወሰን እንደሚገባ ህገ መንግስቱ ራሱ በደነገገው አግባብና በሌሎች አገራት እንደተለመደው የሰበር ችሎቱ የራሱ የሆነ የችሎት አደራጃጀትና ስነ ስርዓት እንዲኖረው ተደርጎ ሲሰራበት እንደቆየና አሁን ባለው የህግ ማዕቀፍም ችሎት ይህንኑ አሰራር በተወሰነ መልኩ በማሻሻል አጠናክሮ መቀጠሉ ይታወቃል፡፡ አሁን ባለው የፌዴራል ፍርድ ቤቶች አዋጅ ቁጥር 1234/2013 የሰበር አቤቱታዎችን ለማጣራት የሚያስችል ሥርዓት ተዘርግቷል። ይህ አዋጅ "የሰበር አጣሪ ችሎት" በመባል የሚታወቀውንና በሦስት ዳኞች የሚዋቀረውን ችሎት በማቋቋም ወደ ባለአምስቱ የሰበር ችሎት የሚቀርቡ አቤቱታዎችን አስቀድሞ በማጣራት "የበር ጠባቂነት" ሚና እንዲጫወት አድርጓል።² አሁን ባለው አሰራር አንድ ጉዳይ ቢያንስ አምስት ዳኞች በሚሰየሙበት የሰበር ችሎት ጉዳዩ ቀርቦና ጉዳዩ ተጠሪን ያስቀርባል ተብሎ በተዘረጋው ስርዓት መሰረት ክርክሩ ተካሂዶ በበታች ፍርድ ቤቶች በተሰጡ ውሳኔዎች መሰረታዊ የሆነ የህግ ስህተት ተፈፅሟል የሚል የችሎቱን ድምዳሜ ማግኘት መቻል እጅግ እየጠበበ የመጣ ጉዳይ ሲሆን ይህ ኩነት የሚጀምረው ደግሞ ከሰበር አጣሪ ችሎቱ ደረጃ ላይ ጀምሮ ነው፡፡ የዚህ ችሎት አይነተኛ ሚና የሰበር አቤታታ የሚቀርብባቸው ጉዳዮች ሁሉ ወደ ባለአምስቱ ዳኞች ሰበር ችሎት እየቀረቡ የስራ ጫና እንዳይፈጠሩ ማድረግ ሲሆን ይህንኑ ሚና ሲወጣ ደግሞ የቀረበው የሰበር አቤቱታ በአዋጁ በአንቀፅ 2(4) ያስቀመጣቸውን የመሰረታዊ ህግ ስህተት መመዘኛዎቹን የሚያሟላ መሆን ያለመሆኑን የሚመረምር ሲሆን በተለይ የሰበር አቤቱታ ከቀረበበት ጉዳይ መሰረታዊ የህግ እና የፍሬነገር ነጥቦች ጋር ተመሳሳይ በሆነ ጉዳይ ላይ በባለአምስቱ ወይም በባለሰባቱ ዳኞች የሰበር ችሎት አስቀድሞ የተሰጠ የህግ ትርጉም ካለ ይህንኑ የማረጋገጥና የባለአምስቱን ዳኞች ሰበር ችሎት ድካም በመቀነስ የባለአምስቱን ዳኞች ሰበር ችሎት የስራ ቅልጥፍናውንና ጥራቱን በማሳደግ ረገድ ተገቢውን አስተዋፅኦ ማበረከት ይጠበቅበታል፡፡ ይህ ሁሉ የሰበር አጣሪ ችሎቱ ሚና ጠቅለል ተደርጎ ሲገለፅ የችሎቱን "የበር ጠባቂነት" ሚና የሚያሳይ ነው ተብሎ ሊወሰድ የሚችል ነው፡፡

1.2. ከላይ ጠቀስ ለማድረግ እንደተሞከረው የሰበር አቤቱታዎችን አስቀድሞ የማጣራት ሥርዓት መዘርጋቱ ከሰበር ስርዓት መሰረታዊ ዓላማ አንፃር ሲታይ ውስን የሆነውን የሰበር ችሎቱን የሰው ሀብት ከፍትሕ ተደራሽነት መብት ጋር ለማመጣጠን የሚያስችል የሰበር ዳኝነት ስርዓት አስተዳደር ጥበብ ተደርጎ ሊወሰድ የሚችል ነው፡፡ እንዲህ አይነት ስርዓትን ቀልጣፋና ውጤታማ ለማድረግ ስርዓቱን የዘረጉት ህጎች ጠንካራና ግልፅ ሁነው ትርጉም ባለው መንገድ እንዲተገበሩ የሚያስችል ተቋማዊ አሰራርና የስራ ዲሲፕሊን እንዲሰፍን ማድረግ የግድ ይላል፡፡ አሁን ባለው የህግ ማዕቀፍና አሰራር የሰበር አጣሪ ችሎትን የሚገዛው ዝርዝር የሥነ-ሥርዓት አሠራር ግን ከባድ የሕግና የተግባር ጥያቄዎችን የሚያስነሳ ሁኖ ይታያል፡፡ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሰበር ሥነ-ሥርዓት መመሪያ ቁጥር 17/2015 አንቀፅ 6(2) አመልካች በአጣሪ ችሎቱ ፊት ቀርቦ በቃል እንዲሰማ ይደነግጋል፡፡ ነገር ግን በተግባር ሲታይ አመልካቹ የተፈጸመውን መሠረታዊ የሕግ ስህተት ለማስረዳት የሚያገኘው የመጨረሻ ዕድል የሆነው ይህ የቃል ክርክር በምንም ዓይነት መልኩ በጽሑፍ አይመዘገብም። ችሎቱ አቤቱታውን ውድቅ ለማድረግ ወይም ወደ ባለአምስቱ ዳኞች የሰበር ችሎት እንዲተላለፍ ለመወሰን የሚሰጠው ትዕዛዝም አመልካቹ በቃል ያቀረባቸውን የክርክር ነጥቦች መሰረታዊ ይዘት ሳያሰፍር ወይም ሳያንጸባርቅ በጥቅሉ የሚተላለፍበት አጋጣሚ በርካታ ነው። ይህ ሁኔታ የሥነ-ሥርዓት እንቆቅልሽን (paradox) ይፈጥራል፡፡ በሕግ እንዲካሄድ የታዘዘ የቃል ክርክር ተደርጎ የቃል ክርክሩ መሰረታዊ ይዘቱ የመዝገቡ አካል ሳይሆን ይታለፋል፤ ወይም ተኖ ይጠፋል። በሕግና በተግባር መካከል ያለው ይህ ክፍተት የግልጸኝነትን፣ በምክንያት የተደገፈ ውሳኔ የማግኘት መብትንና በአጠቃላይ የሰበር ሂደቱን ፍትሐዊነት በተመለከተ ከባድ ጥያቄዎችን የሚያስነሳበት መሆኑ ይታመናል፡፡ በዚህ ችሎት ውድቅ የሚደረግ አቤቱታ የመጨረሻ የዳኝነት ውጤት ያለው በመሆኑ የአመልካችን የፍትሕ ጉዞ ፍጻሜ አብሳሪ መሆኑ ይታወቃል፡፡ እንዲህ ዓይነት የመጨረሻ ውጤት ላለው ውሳኔ መሠረት የሆነው የቃል ክርክር በጽሑፍ አለመመዝገቡ ደገሞ ጥልቅ የሆነ ጥናት የሚያስፈልገው ነው፡፡ ይህ አጭር ፅሁፍ ጥልቅ በሆነ እና ሳይነሳዊ በሆነ መንገድ የተደረገ ጥናት ሳይሆን የፀሃፊውን የስራ ልምድ፤ በአጣሪ ችሎቶቹ ላይ ደንበኞችን በወከለባቸው ጉዳዮች በተለያዩ ቀናት በመገኘት በግል ያስተዋላቸውን እና ከተለያዩ የስራ ባለደረቦች ጋር ስለጉዳዩ በአደረጋቸው ውይይቶች ከባለደረቦቹ የተገኙትን ምልከታዎችን በመረጃነት በመጠቀም የቀረበ ግላዊ የሆነ ሙያዊ አስተያየት ነው፡፡

1.3. ስለሰበር አጣሪ ችሎት በአዋጅ ቁጥር 1234/2021 የተዘረጋው የዳኝነት ስልጣን መዋቅር ባለሁለት ገፅታ ወይም ደረጃ ያለው ስለመሆኑ የችሎቱን ስልጣን ከሚያስቀምጠው የአዋጁ አንቀፅ 28(1) መረዳት ይቻላል፡፡ በዚህ ንዑስ ድንጋጌ እና በንዑስ ቁጥር ሁለት ድንጋጌ መሰረት የችሎቱ የመጀመሪያው ገፅታ ወይም ደረጃ "መሠረታዊ የሕግ ስህተት የለም ብሎ ካመነ አቤቱታውን ውድቅ" የማድረግ ስልጣን ሲሆን ሁለተኛው ጉዳዩ የመሰረታዊ ህግ ስህተት ነጥብ አለው ብሎ ካመነ ጭብጥ በመመስረት ለአምስት ዳኞች ሰበር የመምራት ስልጣን ነው፡፡ ህጉ አንድ የሰበር አቤቱታ በባለአምስቱ ዳኞች የሰበር ችሎት ሊሰማ የሚችለው አስቀድሞ በሦስት ዳኞች ችሎት መሠረታዊ የሕግ ስህተት መኖሩ ላይ ብይን ሲሰጥበት ብቻ መሆኑን መደንገጉ ከላይ ስለችሎቱ በር ጠባቂነት የተጠቀሰውን ሚና የሚያሳይ ሲሆን ይህንኑ ስልጣን ተጠቅሞ ደግሞ ችሎቱ ከላይ ከተገለፁት ሁለት ዓይነት ደረጃዎች አንዱን ውሳኔ ሊሰጥ ይችላል፡፡ በህጉ ተለይቶ የተቀመጠው አስራር አጣሪ ችሎቱን ከበር ጠባቂ ወይም ቅድመ ምርመራ አካል ጋር የሚያመሳስል አይነት አካሄድ ነው ቢባልም ችሎቱ ጉዳዩን መርምሮ መሰረታዊ የህግ ስህተት የለበትም በማለት መዝገቡን በመዝጋት የሚሰጠው ውሳኔ በአገሪቱ የዳኝነት ስርዓት ውስጥ የመጨረሻ ውጤት ያለው በመሆኑ ህግ አዋጪው ለችሎቱ እጅግ ከፍተኛ የሆነ የዳኝነት ስልጣን የሰጠው መሆኑን የሚያሳይ ነው፡፡

1.4. የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የራሱን የሰበር ስነ ሥርዓት ለመደንገግ ያወጣው መመሪያ ቁጥር 17/2015 ወሳኝ የሆነ ድንጋጌ ይዟል። የመመሪያው አንቀጽ 6(2) "የሰበር አጣሪ ችሎቱ ... ከመወሰኑ በፊት አቤቱታው የሚሰማበትን ቀን በመወሰን አመልካቹን መስማት አለበት" በማለት በግልጽ ያስቀምጣል። ሆኖም መመሪያው ይህ የቃል ክርክር "እንዴት" መካሄድ እንዳለበት—በተለይም የቃል ክርክሩ በጽሑፍ መመዝገብ እንዳለበት ዝምታን መርጧል። አሁን በሰፊው በመተግበር ላይ ያለው የችሎቱ አሰራር ዋነኛ ችግር የሚመነጨውም ከዚሁ የመመሪያው ዝምታ ነው። ድንጋጌው በጽሑፍ የቀረበውን አቤቱታ ብቻ መርምሮ መወሰንንም አይፈቅድም፡፡

1.5. ከችሎት ምልከታ የተገኙ ተጨባጭ መረጃዎች የሚያሳዩት የአጣሪ ችሎት አሰራር ወጥ መሆኑ ሲሆን መዝገቡን የያዘው የችሎቱ ዳኛ በአብዛኛው ጽሑፍ አቤቱታውን በማጠቃለል ለአመላካቹ/ጠበቃው ከተገለፀ በኋላ ቀጥሎም አመልካች (ወይም ጠበቃው) የሥር ፍርድ ቤት ውሳኔ "መሠረታዊ የሕግ ስህተት" የያዘው ለምን እንደሆነ በቃል እንዲያብራራ ዕድል ይሰጠዋል። አመልካቾችም ብዙውን ጊዜ ጉዳያቸውን በስሜት ጭምር እንደገና በማቅረብ ቁልፍ የሕግ ነጥቦችን ለማስረዳት ይሞክራሉ። ከአምስት እስከ አሥር ደቂቃ በሚወስደው በዚህ የቃል ክርክር ወቅት ዳኞቹ በትኩረት ሲያዳምጡ ቢታዩም ማስታወሻ ሲይዙ ወይም የክርክሩን ይዘት በይፋዊ መንገድ ሲመዘግቡ ግን አይታዩም። ክርክሩ ካለቀ በኋላ ችሎቱ ለሁለት ወይም ለሶስት ቀናት፣ ቢበዛ ደግሞ ለሳምንት ቀጠሮ ይሰጥና በእነዚህ ቀናት ውስጥ ዳኞቹ ተመካክረው አቤቱታው ወደ ባለአምስቱ ዳኞች ሰበር ችሎት መተላለፉን ወይም በአብዛኛው እንደሚሆነው ውድቅ መደረጉ በግልፅ ችሎት ይገልጻል። በአመልካቹ የቀረበውን ወሳኝ የቃል ክርክር ግን እንኳንስ ሙሉ በሙሉ ተመዝግቦ ሊገኝ ይቅር ዱካውም አይገኝም፡፡ የቃሉ ክርክሩ ዱካ ለማግኘት የሚዳግተው በተዘጉ መዝገቦች ብቻ ሳይሆን ወድ ባለአምስቱ ዳኞች ሰበር ሰሚ ችሎት እንዲተላለፉ በሚደረጉ መዝገቦች ጭምር መሆኑን በርካታ የችሎቱ መዝገቦች ያሳያሉ፡፡

1.6. ስለጉዳዩ የአጣሪ ችሎት ዳኞች ያላቸውን እይታ ስንመለከትም አሁን ተግባራዊ እየሆነ ባለው አሠራር ወጥ የሆነ ምክንያት የሚያቀርቡ መሆኑ ነው፡፡ የችሎቱ ዳኞች ዋንኛ ትኩረት በ ቅልጥፍና (efficiency) ላይ ያነጣጠረ ነው። በችሎቱ ለረዥም አመታት የሰሩ ዳኞች በዚህ ረገድ የሚያቀርቡት ማብራሪያ "በቀን በርካታ መዝገቦችን እንዲያዩ እንደሚደረግ፣ የቃል ክርክሩ ዓላማም የአመልካቹን ዋነኛ ብሶት/የፍትህ በደል በፍጥነትና በፅሁፉ ላይ እንደሰፈረው በትክክል ለመረዳት ነው... እያንዳንዱን ቃል መመዝገብ የማጣራት ሂደቱን ወደ ሙሉ የፍርድ ሂደት ይቀይረዋል፤ ይህም የሥርዓቱን ዓላማ ያሳጣል።" የሚል ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የችሎቱ ዳኞች የቃል ክርክሩ እንዳለቀ ክርክሩ በአዕምሯቸው ውስጥ ትኩስ እያለ/ሳይረሳ ውይይት ስለሚያደርጉ የጽሑፍ መዝገብ አስፈላጊ ሆኖ እንደማይሰማቸው በምክንያት ሲያቀርቡ ይሰማል፡፡ የችሎቱ ዳኞች ሚናቸውን የሚገነዘቡት የመሰረታዊ ሕግ ስህተትን እንደመለየት እንጂ ውድቅ ለሚደረግ ክርክር ሁሉን አቀፍ መዝገብ እንደመፍጠር አይደለም።

1.7. የሕግ ባለሙያዎች እይታ ሲታይ ደግሞ በከፍተኛ ቅሬታ የተሞላ ሁኖ ይገኛል፡፡ ብዙዎቹ ጠበቆች ሂደቱን "ወደ ባዶ ስፍራ እንደ መጮኽ" ወይም አየር ላይ እንደ መተኮስ ነው ሲሉ ይገልፁታል። እንዲሁም ጠበቆቹ "ውስብስብ የሆነ የሕግ ስህተትን ለማስረዳት በጥንቃቄ እንደሚዘጋጁና በተፈቀደላቸው የሰዓት ገደብ ውስጥም እንደሚናገሩ፣ ዳኞቹም እንደሚያዳምጧቸው ከጠቀሱ በኋላ በአጭር ቀናት ውስጥ በተሰጣቸው ቀነ ቀጠሮ ቀርበው አቤቱታቸው ውድቅ መደረጉን የሚገልጽ ባለአንድ-መስመር ትዕዛዝ ተቀብለው እንደሚመለሱ ሲገልፁ ይታያሉ፡፡ ጠበቆቹ በቃል ያቀረቧቸው ነጥቦች ግምት ውስጥ መግባታቸውን ይቅርና ለምን ውድቅ እንደተደረጉ እንኳ ሊያውቁ የሚችሉበት መንገድ እንደሌለም ይገልፃሉ። ከዚህ በመነሳትም እንዲህ አይነት የዳኝነት አካሄድ 'ፍትሕ መታየትም አለበት' የሚለውን መርህ የሚሸረሽር መሆኑ ሲሉ ይደመድማሉ። ጥቂት የማይባሉ ጠበቆ ደግሞ የቃል ክርክሩ በጽሑፍ ተመዝግቦ የመዝገቡ አካል ያለመሆን ሂደቱን እጅግ ግላዊ (subjective) እንደሚያደርገውና የችሎቱን ውሳኔ ከማንኛውም ዓይነት ቁጥጥር እንደማያላቅቀው ሲጠቀሱ ይታያል፡፡

1.8. ችሎቱ አሁን እየተገበረው አሠራር ከሕግና ከሕገ-መንግሥታዊ መርሆዎች አንጻር ሲተነትንም በርካታ መብቶችን ያለማክበር አዝማሚያ የሚስተዋልበት ሁኖ ይታያል፡፡ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ሕገ-መንግሥት አንቀጽ 37(1) ማንኛውም ሰው "ፍትሐዊና ግልጽ በሆነ የፍርድ ሂደት" የመዳኘት መብት እንዳለው ያረጋግጣል። አገሪቱ ያፀደቀቻቸው እንደ ሲቪልና ፖለቲካዊ መብቶች ቃል ኪዳን (ICCPR) እና የአፍሪካ የሕዝቦችና የሰብዓዊ መብቶች ቻርተር(AfCPHR) ያሉት ዓለም አቀፍ ስምምነቶችም ፍትሃዊና ግልፅ በሆነ የፍርድ ሂደት የመዳኘት መብትን የሚጠብቁ ድንጋጌዎችን ይዘው ይገኛሉ፡፡ ከህገ መንግስቱ ድንጋጌም ሆነ ከተጠቃሾቹ አለም አቀፍ ስምምነቶች ድንጋጌዎች ይዘትና መንፈስ ጋር በሚጣጣም መልኩ አዋጅ ቁጥር 1234/2013 በአንቀፅ 32 እንዲሁም አዋጅ ቁጥር 1233/2013 በአንቀፅ 37 ስር መብቱን የሚጠብቁ ድንጋጌዎችን አስፍረው እናገኛለን፡፡ እንዲሁም የህገ መንግስቱ አንቀፅ 12 እና ስራ ላይ ያሉት መረጃ የማግኘት መብትን የሚጠብቁ ህግጋት ሲታዩም ግልፀኝነትን፣ ተጠያቂነትን እና መልካም አስተዳደር ከማስፈን አንፃር ሲታይ በህግ ክልከላ ከተደረገላቸው መረጃዎች በስቀር አንድ ሰው ስለጉዳዩ የተሟላ መረጃ የማግኘት መብት ያለው መሆን እንዳለበት የሚያስገነዝቡ መሆናቸው ተጠቃሹ መብት በበርካታ ህግጋት ጥበቃ የተደረገለት ትልቅ መብት መሆኑን ነው፡፡ ከእነዚህ ህግጋት ይዘትና መንፈስ አንፃር ሲታይ በአጣሪ ችሎቱ የሚካሄደው የቃል ክርክርና የውጤት አገላለፅ ሂደት ይፋዊ ቢሆንም ፍትሐዊነቱ ግን አጠያያቂ ነው። ፍትሐዊ ችሎት ማለት ለውሳኔ መሠረት የሆኑ ሂደቶች የሚመዘገቡበት ግልጽ ሥርዓትንም የሚጨመር ስለመሆኑ አከራካሪነት ያለው አይመስልም። የአውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ፍርድ ቤት ልምድ ሲታይም አንድ ችሎት በእውነት ፍትሐዊ ለመሆን ተከራካሪው ያቀረባቸው ማስረጃዎችና ክርክሮች በአግባቡ ግምት ውስጥ መግባታቸውን እንዲተማመንበት የማድረግ ግዴታ እንዳለበት በተደጋጋሚ በሰጣቸው ውሳኔዎች የሚያረጋግጡ ስለመሆኑ በርካታ የምርምር ስራዎችና የድረ ገፅ መረጃዎች ይመሰክራሉ፡፡ አጣሪ ችሎቱ አሁን ባለው የህግ ማዕቀፍ የመጨረሻ የዳኝነት ውሳኔ የመስጠት ስልጣን ያለው አካል እንደመሆኑ መጠን ወደዚህ አካል የሚቀርበው አንድ የቃል ክርክር ሳይመዘገብ መቅረቱ ወሳኝ የሆነውን የዳኝነት ሂደት ክፍል ሚስጥራዊነት የሚያዳፍነው ነው፡፡ የችሎቹ አሰራር ከላይ የተጠቀሱት ህግጋት የሚጠብቁትንና እንደአውሮፓ የሰብአዊ መበቶ ፍ/ቤት ያሉት ተቋማት ከአረጋገጡት መሰረታዊ መርህ አንፃር ይ የዳበረ የዳኝነት ስርዓት ያላቸው አገራት ከመጨረሻው የዳኝነት አካል የሚጠበቅ ግዴታ ነው በማለት ተግባራዊ መሆን አለበት በሚል ከሚጠብቁት መሰረታዊ ሰብአዊ መብት አንፃር ሲፈተን ምንም አይነት የህግ ድጋፍ ሊቀርብለት የሚችል አይደለም፡፡

1.9. የችሎቱ አሰራር በምክንያት የተደገፈ ውሳኔ ከማግኘት መብት አንፃር ሲታይም ተቀባይነት የሌለው ሁኖ ይገኛል፡፡ በምክንያት የተደገፈ ውሳኔ የማግኘት መብት የሕግ የበላይነት የማዕዘን ድንጋይ ሲሆን የዳኝነት ውሳኔዎች የዘፈቀደ እንዳይሆኑ ያረጋግጣል። ይህ መብት ፍትሐዊ የፍርድ ሂደት የማግኘት መብት ውስጥ በተዘዋዋሪ የተካተተ ሲሆን በእኛ አገር መረጃን ጥበቃ በሚያደርጉና ስራ ላይ ባሉ ህጎችም የተጠበቀ ነው፡፡ አጣሪ ችሎቱ አንድን የሰበር አቤቱታ ውድቅ በማድረግ በሚሰጠው የጽሑፍ ትዕዛዙ እና ቀድሞ በሰፊው ሲሰራበት በነበረው አሰራር በሁሉም መዝገቦች ላይ "አቤቱታውን በመመርመር መሠረታዊ የሕግ ስህተት አለመኖሩን ችሎቱ ተረድቷል" የሚል ቀመር-ተኮር ሐረግ ብቻ አስፍሮ መዝገቡን ይዘጋ ነበር። ከሰበር ችሎቱ የስነ ስርዓት መመሪያ መውጣትና መተግበር ከተጀመረ በኋላ በአዋጁ አንቀፅ 28(1) አግባብ በሚሰጠው ውሳኔ ለውሳኔው ምክንያት የሆኑትን ነጥቦች በፅሁፍ ማስፈር እንዳለበት መመሪያው በአንቀፅ 6(3) ስር ከሚያስገድደው ውጪ የመጨረሻ የሆነውን ዳኝነት ሲሰጥም ሆነ ጉዳዩን ወደ ባለአምስቱ ዳኞች ሰበር ችሎት ሲያስተላልፍ በቃል ክርክር ጊዜ የቀረቡ የህግ መከራካሪያ ነጥቦችን በውሳኔው ውስጥ የማስፈር ህጋዊ ግዴታ አልተጣለበትም፡፡ አጣሪ ችሎቱ የሚመራው አግባብነት ባላቸው የአዋጁና የሰበር ስነ ስርዓት መመሪያ ድንጋጌዎች ሲሆን በገዛ መመሪያው እንዲካሄድ የታዘዘውን የቃል ክርክር ይዘት ሙሉ በሙሉ ወደ ጎን በመተው በፅሁፍ የሚያስፍራቸው ምክንያቶች የተሟሉ ናቸው ሊባል አይቻልም፡፡ ከሁሉም በላይ ለሰበር ችሎቱ የሚቀርበው መሰረታዊ የህግ ስህተትን የሚያሳይ የሰበር አቤቱታ ክፍል የጉዳዩች ልዩ ባህርይ ግንዛቤ ውስጥ ሳይገባ በሶስት ገፅ የተገደበ ከመሆኑ አንፃር ሲታይ በቃል ክርክር ጊዜ የሚቀርበውን ማብራሪያ ያለመመዝገብና በውሳኔው ውስጥም እንዲካተት ያለማድረግ የችሎቱን የፍርድ ሂደት ግልፅኝነትና አሳማኝነት የሚጎዳ ነው፡፡ በቃል ክርክር ጊዜ የቀረበ ማብራሪያ በውሳኔው እንዲካተት ያለማድረግ የሰበር አመልካቹ ክርክሩ ችሎቱን ለምን እንዳላሳመነ ለመገመት ያዳግተዋል፡፡ ይህ አሠራር የዳኝነት አካላት ለውሳኔዎቻቸው ምክንያት የመስጠት ግዴታቸው ጋር የሚጋጭ ነው፡፡ ምክንያት የተደገፈ ውሳኔ የመስጥዕት ግዴታ ደግሞ ለሕዝብ አመኔታና ለዳኝነት ስራ ተገማችነት እጅግ አስፈላጊ ነው።

1.10. የችሎቱ አስራር ከፍትሕ ተደራሽነት መርህ አንፃር ሲታይም ችግር ሊያመጣ የሚችልበት አጋጣሚ መኖሩን የሚያስገነዝብ ነው፡፡ አጣሪ ችሎቱ የተቋቋመበት ዓላማ የመሰረታዊ ሕግ ስህተት ላላቸው ጉዳዮች ወደ ባለአምስቱ ዳኞች ሰበር ችሎት የሚያደርጉትን ሂደት ለማቀላጠፍ ነው ቢባልም ተግባራዊ በመደረግ ላይ ያለው አሠራሩ ግን ከወዲሁ ሊታይ የማይችል ችግር ሊያመጣ ይችል ይሆናል። የፍትሕ ተደራሽነት ማለት ክስ የመመሥረት መብት ብቻ ሳይሆን በህጉ አግባብ የተመሰረተው ክስ ፍትሐዊና ግልጽ በሆነ ሥርዓት ውሳኔ የማግኘት መብትንም እንደሚጨምር የህጉ ፍልስፍና የሚቀበለው ጉዳይ ነው፡፡ የቃል ክርክርን ሳይመዘግብና በዚህ የክርክር ደረጃ ለቀረቡት ነጥቦች ምላሽ ሳይሰጥ በማለፍ የሚሰጥ ዳኝነት ሥርዓቱ የዘፈቀደነት አሰራር ያለው መሆኑ ማሳይ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል፡፡ ይህም በፍትሕ ሥርዓቱ ላይ ያለውን የሕዝብ አመኔታ ሊሸረሽርና ዜጎች ለእውነተኛ የሕግ ስህተቶች መፍትሔ ከመፈለግ ይልቅ ህጋዊ ሂደቱን ያልተከተለ ሌላ አማራጭ ወደመፈለግ እንዲያዘነብሉ ሊያደርግ ይችላል። በህጉ የግድ እንደሆኑ የተቀመጡትን ሂደቶች በሚገባ ባለመመዝገብ የሚገኘው የዳኝነት ስራ ቅልጥፍና ውጤታማነት እጅግ መሰረታዊ የሆኑ መብቶች ላይ ከፍተኛ ጉዳት የሚያስከትል በመሆኑ ቡራኬ የሚያገኝበት የህግም ሆን የአመክንዮ ድጋፍ የለውም፡፡ በሌላ አገላለፅ የቃል ክርክር ማስማት የግድ ስለመሆኑ ስራ ላይ ያለው ህግ ያሳያል ከተባለ ችሎቱ ካለው የስራ ብዛት በመነሳት ለቅልጥፍና በሚል ሰበብ መነሻ በዚህ ሂደት የሚቀርበውን የቃል ክርክር ሳይመዝገቡና የውሳኔው አካል ሳያደርጉ ማለፍ የፍሬ ነገርና የሥነ-ሥርዓት ፍትሕን አደጋ ላይ ሊጥል እንደሚችል ይታመናል፡፡ ይልቁንም ምንም ጥቅም ላይ የማይውል የቃል ክርክር ለማድረግ ለተከራካሪዎች ጊዜ ሰጥቶ በሁሉም መዝገቦች ላይ መስማት የችሎቱን ውድ ጊዜ እና ጉልበት በማባከን በቅልጥፍናው ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እንደሚያስከትል ይታመናል፡፡ ችሎቱ ትርጉም የሌለውን የቃል ክርክር ሲያከናውን ስለሚውል በቀጠሮው ሰዓት የሚስተናገድ ባለጉዳይ የለም፡፡ የሚገርመው ደግሞ ምንም የህግ እውቀት የሌላቸውና በጠበቃ ያልተወከሉ አመልካቾች ጭምር በጉዳዩ ላይ መሰረታዊ የሆነ የህግ ስህተት ተፈፅሟል የሚሉበትን ምክንያት በቃል እንዲያስረዱ እድል ተሰጥቶአቸው ችሎቱ በቃል ሲሰማ የሚታየበት አጋጣሚ መኖሩም ነው፡፡ በአጠቃላይ ፋይዳ የሌለውን የቃል ክርክር ከባለሙያም፣ ባለሙያ ካልሆነው ባለጉዳይም ጭምር ሲሰሙ እየዋሉ የቃል ክርክሩ የማይመዘገበው ለቅልጥፍ ተብሎ ነው የሚለው ምክንያት የዳኝነት ስራ ቅልጥፍና የሚለካበትን ሳይንሳዊ መሰፍርቶች ምን ምን እንደሆን ያላገናዘበ እና የችሎቱን የስራ ብዛት የሚያቃልልን መስፈርት ብቻ ነጥሎ በመውሰድ የታሰበ በመሆኑ አሳማኝነት የጎደለው ነው፡፡ የዳኝነት ስራ ቅልጥፍ የሚለካው የተገልጋዩ እርካታና ሌሎች በርካታ መመዘኛዎችን ጥቅም ላይ በማዋል ስለመሆኑ ይታወቃልና፡፡

1.11. ይህ አጭር፣ ጉዳዩን በጥልቀትና ሳይንሳዊ በሆነ የምርምር ስራ ሳይካሄበት በፀሃፊው ምልክታና ሳይንሳዊ ባልሆኑ የመረጃ አሰባሰብ መንገዶች የተፃፈ ፅሁፍ በሰበር አጣሪ ደረጃ በሕግ በግዴታነት የተቀመጠውን የቃል ክርክር የማካሄድ ሥርዓት እና የዚያኑ ክርክር በይፋዊ መዝገብ ላይ ያለውን ተጨባጭ ፋይዳ በተመለከተ በርካታ ችግሮች እንደሚታዩና ሊኖሩ እንደሚችሉ በመጠኑም ቢሆን ለማንሳት ጥረት አድርጓል፡፡ ለሰበር የዳኝነት ስርዓት ቅልጥፍና፣ ውጤታማነትና ጥራት ተብሎ የተነደፈው የአጣሪ ችሎት(አሁን ያለውን የዚህን ችሎት አጠቃላይ አሰራርና ይህንኑ ዓላማውን የማሳካት ያለማሳካቱ ጉዳይ ሌላ ጥልቅ ሳይንሳዊ ጥናት የሚያስፈልገው መሆኑ እንደተጠበቀ ሁኖ) የፍትሐዊነትን፣ የግልጸኝነትን እና በምክንያት የተደገፈ ውሳኔ የማግኘት መብትን የሚሸረሽር የሥነ-ሥርዓት ክፍተት ይዞ በመስራት ላይ እንደሚገኝ ይታመናል፡፡ ይኸው የሰበር ችሎት እንደ ዳኝነት ተቋምነቱ አሁን ተግባራዊ እያደረገ የሚገኘውን የቃል ክርክር ያለመመዝገብና በውሳኔው ውስጥ በሚገባ ያለማካተት ችሎቱ ካለው የስራ ጫና መነሻ በማድረግ በቅልጥፍና እና በውጤታማነት መነጽር ለመከላከል እንደሚነሳ ቢገመትም የሕግ በባለድርሻ አካላትና በተገልጋዩ ማህበረሰብ የሚንፀባረቁት ስሜቶች እና ከላይ የተጠቀሱት ሕገ-መንግሥታዊ መርሆዎች ግን በዳኝነት አስተዳደሩ ላይ ችግር ሊያስከትል እንደሚችል ይጠቁማሉ፡፡ በመሆኑም በፌ.ጠ.ፍ.ሰ.ሰ.ች የሰበር አጣሪ ችሎት ተግባራዊ እየሆነ ያለው የቃል ክርክር አመራር ስርዓት ከሕገ-መንግሥታዊ የፍትሃዊ የፍርድ ሂደት መብት ጋር ሙሉ በሙሉ የተጣጣመ አይደለም። የግዴታ የሆነው የቃል ክርክሩ በጽሑፍ አለመመዝገቡ በዳኝነት ሂደት ውስጥ ፋይዳ የሌለውን ሂደት በመፍጠር፣ ወሳኝ የሆነውን የሥርዓት ክፍል የማይታይና ተጠያቂነት የጎደለው አድርጎታል፡፡ በማናቸውም ደረጃ የዳኝነትን የሥራ ጫና የማስተዳደር ዓላማ ተገቢ ቢሆንም፣ ለዳኝነት አካሉ ህጋዊነትን የሚሰጡትን መሠረታዊ መርሆዎች መሥዋዕት በማድረግ ግን ቅልጥፍና እና ውጤታማነት ሊሳካ አይገባም።

1.12. ሲጠቃልለም አሁን ላለው ችግር የመፍትሄ ሀሳቦች ሊሆኑ ከሚችሉት አንዱ በሰበር ስነ ስርዓት መመሪያ አንቀጽ 6 ስር ያለውን ድንጋጌ በማሻሻል በአጣሪ ችሎቱ ፊት የሚቀርቡ የቃል ክርክሮች ቢያንስ በድምፅ እንዲቀረጹ፣ ወይም መሰረታዊ ነጥቦችን በእጅ መመዝገብ የግድ ስለመሆኑ በግልጽ እንዲደነግግ ማድረግ ነው ተብሎ ሊጠቀስ ይችላል፡፡ ይህም ለእያንዳንዱ ጉዳይ ሙሉ የጽሑፍ ግልባጭ የማዘጋጀት ጫና ሳያስከትል ይፋዊና ህጋዊ የሆነ የተሟላ መዝገብ እንዲኖር ያደርጋል። እንዲሁም መመሪያው የአጣሪ ችሎቱ ለሰበር ችሎቱ አይቀርቡም የሚል ዳኝነት በሚሰጣቸው መዝገቦች ላይ አመልካቹ በቃል ያቀረባቸውን ዋነኛ የህግ ክርክሮች ጭምር በአጭሩ በመጥቀስ ለምን መሠረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት እንዳልሆኑ እንዲገልጽ በሚያስገድድ መልኩ ሊሻሻል ይገባል። ከእነዚህም በተጨማሪ መመሪያው በይፋ እስከሚሻሻል ድረስ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ የአጣሪ ችሎት ሰብሳቢ ዳኞች ወይም ጉዳዩን ያነበበና የሚሰማው የችሎቱ ዳኛ አመልካቹ ያቀረበውን የቃል ክርክር አጭር ማጠቃለያ ጽፈው በግልፅ የመዝገቡ አካል እንዲያደርጉ የሚያስገድድ የመግባቢያ ሰነድ ወይም የውስጥ መመሪያ ቢያወጣ ችግሩን በመጠኑም ቢሆን ሊቀንስ ይችላል፡፡ አጣሪ ችሎቱ አንድን ጉዳይ ወደ ባለአምስቱ የሰበር ችሎት ሲመራው የመሰረተው ጭብጥ በአመልካቹ በፅሁፍ ከቀረበው የሰበር አቤቱታው ላይ በግልፅ ያልተቀመጠ ሆኖ በቃል ክርክር ጊዜ በቀረበ ማብራሪያ ችሎት የተገነዘበውና ከመሰረታዊ የሰበር ቅሬታ ነጥቦች ጋር በይዘቱ የሚጣጣም ከሆነ የጭብጡን ምንጭ የሚያሳይ በቃል ክርክር ጊዜ የተመዘገበ ሰነድ የመዝገቡ አካል የሚያደርግበትን የአሰራር ስልት መቀየስ መቻልም ለባለአምስቱ የጉዳይ አመራርም ሆነ በውጤቱ ላይ መልካም ተፅእኖ ሊያስከትል እንደሚችል ይገመታል፡፡ እንዲሁም የቴክኖሎጂ አማራጮችን መፈተሽም የሚመከር ነው፡፡ አሁን እየተስፋፋ ካለው የቴክኖሎጅ መሰረተ ልማት አንፃር የዳኝነት አካሉ ለሰበር አጣሪ ችሎቱም በየችሎት ክፍሎች ውስጥ ቀላልና ወጪ ቆጣቢ የሆነ የዲጂታል ድምፅ መቅረጫ ቴክኖሎጂ እንዲሟላ ማድረግ ቢያደርግ መልካም ይመስላል፡፡ ሌሎች ከአጣሪ ችሎቶች ብዛት፣ የጉዳዮች ቀጠሮ አያያዝና ተያያዥ ከሆኑ ምክን ያቶች ጋር ተያይዘው የሚከናውኑ ማሻሻያዎችም ለችግሩ እንደ መፍትሄ ሊጠቀሱ ይችላሉ፡፡

The content of this article is intended to provide a general guide to the subject matter. Specialist advice should be sought about your specific circumstances.

[View Source]

Mondaq uses cookies on this website. By using our website you agree to our use of cookies as set out in our Privacy Policy.

Learn More