ARTICLE
3 March 2026

የአስገዳጅ የህግ ትርጉም "ፓራዶክስ"፦ የዳኝነት ነክ ሥልጣን የተሰጣቸው አካላት የፌ/ጠ/ፍ/ቤት ሰ/ሰ/ችሎት አስገዳጅ የህግ ትርጉም ያስገድዳቸዋልን?

5A Law Firm LLP

Contributor

5A Law Firm LLP is Ethiopia's only law firm founded entirely by former judges, with 114+ years of combined judicial and legal experience. Based in Addis Ababa — Africa's diplomatic capital — we advise foreign investors, multinationals, and international organizations on investment law, corporate transactions, tax, arbitration, and regulatory compliance.
1.1. ፍትሐዊ እና ሥርዓት ያለው ማኅበረሰብን ለመገንባት በሚደረግ ጥረት ውስጥ የህግ ወጥ አፈጻጸም እንደ መሠረታዊ መርህ የሚታይለት ነገር ጥቂት
Ethiopia Litigation, Mediation & Arbitration

1. መግቢያ

1.1. ፍትሐዊ እና ሥርዓት ያለው ማኅበረሰብን ለመገንባት በሚደረግ ጥረት ውስጥ የህግ ወጥ አፈጻጸም እንደ መሠረታዊ መርህ የሚታይለት ነገር ጥቂት ነው፡፡ አንድ የህግ ሥርዓት ወጥነት ባለውና በተናበበ መንገድ ሲፈፀም ተገማችነትን ያሰፍናል፣ እኩልነትን ያረጋግጣል፣ የህግ የበላይነትንም ያጠናክራል ተብሎ ይታመናል፡፡ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ (ኢ.ፌ.ዲ.ሪ) በህገ-መንግስታዊ ቅርፅ እና ይዘቱ ይህንን ወጥነት የማረጋገጥ የመጨረሻውን ኃላፊነት ለፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሰጠ ሲሆን፣ የሰበር ሰሚ ችሎቱ በማንኛውም የመጨረሻ የፍርድ ውሳኔ ላይ የሚገኝን "መሠረታዊ የህግ ስህተት" እንዲያርም ሥልጣን ሰጥቶታል።

1.2. ይህ አሠራር በንድፈ-ሀሳብ ደረጃ የሀገሪቱን የዳኝነት ሥርዓት እንደ ምርኩዝ ሆኖ የሚያገለግልና ከሀገ መንግስት ትርጉም በመለስ ባሉት የሌሎች ህጎች ትርጉም አሳማኝነት በሌላቸው በተለያዩ ምክንያቶች በተለያዩ ተቋማዊ ወይም አካባቢያዊ ዘዬዎች የተዘበራረቀ እንዳይሆን የማድረግ ኃይል ይኖረዋል ተብሎ የሚታመን ነው፡፡ ህግ መንግስቱ ሲረቀቅ የነበሩት ውይይት ሰነዶች የሚመስክሩትም ይህንኑ ነው፡፡ ይህንን ህገ-መንግስታዊ ርይዕ ወደ ተግባር ለመለወጥ ቀድሞ የወጣው አዋጅ ቁጥር 454/1997'ም' ሆነ ይህንኑ አዋጅም ሆነ ሌሎች ተያያዥ አዋጆችን በመተካት ስራ ላይ ያለው የፌ/ፍ/ቤቶች አዋጅ ቁጥር ፩ሺ፪፻፴፬/፪ሺ፲፫ አስገዳጅነት ያለው የህግ ትርጉም ሥርዓትን ዓላማና ግብ ምን እንደሆነ በግልፅ ያስቀመጠ ይፋዊ የህግ አውጪ ሀሳብ የሚያሳይ ድንጋጌ ባይዝም ስርዓቱን ቀደሞ ከነበረው የህግ ማዕቀፍ በበለጠ ሁኔታ ለማጠናከር የሚያስችል ህጋዊ ማዕቀፍ ይዟል፡፡ ሆኖም ግን የዚህ አዋጅ ቁልፍ ድንጋጌ የሆነውን አንቀጽ ፲(፪) በጥልቀት ስንመረምር የምናገኘው አንድ ወጥ መርህን ሳይሆን ከፍተኛ ክፍተት ያለው ሆን ተብሎ የተፈጠረ ክፍፍልን ነው፡፡

1.3. የአዋጁ የእንግሊዝኛ ቅጂ "በሰበር ሰሚ ችሎት የሚሰጥ የህግ ትርጉም... ውሳኔው ከተሰጠበት ቀን ጀምሮ አስገዳጅ ይሆናል" በሚል የተቀመጥ ሁኖ የሚታይ ሲሆን ይኸው ይዘት አስገዳጅ የህግ ትርጉም ስርዓቱ ሁሉን አቀፍ የሚመስል መርህን እንደያዝ የሚያስገነዝብ ነው ተብሎ ሊወሰድ የሚችል ይመስላል፡፡ ነገር ግን በአዋጅ ቁጥር 3/1987 አግባብ የበላይነት ያለው የአማርኛው ቅጂ ወሳኝ የሆነ ልዩነት በማሳየት የአስገዳጅ የህግ ትርጉሙን አድማስ ገደብ አድርጎ ይነበባል፡፡ ይኸውም የህግ ትርጉም አስገዳጅነት የሚኖረው "በየትኛዉም ደረጃ በሚገኝ የፌዴራልም ሆነ የክልል ፍርድ ቤት" ላይ መሆኑን በግልጽ ይደነግጋል። በእኔ አረዳድ ይህ በቸልተኝነት የተፈጠረ ስህተት አይደለም፤ ሆን ተብሎ በህግ አውጪው የተደረገ የማግለል ተግባር እንጂ፡፡ ህጉ በኢትዮጵያ መደበኛ ፍርድ ቤቶች እና ሰፊና ከጊዜ ወደ ጊዜ ተጽዕኖ ፈጣሪ እየሆኑ በመጡ የዳኝነት ነክ ሥልጣን በተሰጣቸው አስተዳደራዊ አካላት (tribunals) መካከል የግንብ አጥር ያቆመ ነው፡፡

1.4. በየትኛውም እርከን የሚገኙ መደበኛ ፍ/ቤቶቹ በአስገዳጅ የህግ ትርጉም ተዋረድ ውስጥ ሲታሰሩ፣ ከግብርና ታክስ እስከ ሲቪል ሰርቪስ ሰራቶች፣ እና ከሽማቾች ጥበቃና ከንግድ አሠራሮች እስከ የከተማ ቦታ የማስለቀቅ ድረስ ባሉ ጉዳዮች ላይ የመጨረሻ ውሳኔ የሚሰጡት የዳኝነት ነክ አካላት ግን ከሰበር ሰሚ ችሎቱ አስገዳጅ የህግ ትርጉም ስርዓት ማዕቀፍ ውጪ በህግ ተገልለዋል፡፡ ይህ አጠር ያለ ምልከታ የሆነው ፅሑፍ በዚሁ የህግ ይዘት ላይ ያለውን ፓራዶክስ በአጭሩ ለመዳሰስ የተሞከረበት ነው፡፡

1.5. ምልክታው እነዚህ አካላት የዳኝነት ስልጣኑ እንዲኖራቸው ከተደረገበት ቴክኒካዊ አመክንዮ ጋርም የማይጣጣም (ምክንያቱ የፍሬ ነገር ላይ እነዚህ የሚሰጡት ውሳኔ በይግባኝም ሆነ በሰበር የማይታረም መሆኑን ያስተውሏል)፤ ሆን ተብሎ የዳኝነት ነክ ሥልጣን ያላቸው አካላት ከፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት አስገዳጅ የህግ ትርጉም ውጪ መደረጋቸው የኢትዮጵያ የህግ መዋቅር መሠረታዊ ክፍተት መሆኑን ለመሞገት ጥረት የተደረገበት ነው፡፡ ይህ አሠራር ህገ-መንግስታዊ አለመጣጣምን የሚፈጥር፣ የህግ የበላይነትን ቁልፍ መርሆች የሚሸረሽር እና በመጨረሻም የፍትሕ አስተዳደሩን የሚያዳክም ስርዓታዊ ብቃት ማነስን የሚያሰፍን ነው፡፡ ይህ ሥራ የህግ ማዕቀፉን በመተንተን፣ በፀሃፊውና ከፀሃፊው ጋር የግል ውይይት ከአደረጉ የህግ ባለሙያዎች ተሞክሮ አማካኝነት በተግባር ያለውን ተጽዕኖ በመመርመር፣ በንጽጽራዊ ትንተና ዓለም አቀፋዊ ይዘቱን በማስቀመጥ እና በተረጋገጡ የህግ ንድፈ-ሀሳቦች ላይ ተመስርቶ ሂሳዊ ዳሰሳ ያቀርባል፡፡ በመጨረሻም፣ ችግሩን ከመመርመር ባሻገር ለኢትዮጵያ ይበልጥ የተቀናጀና ወጥ የዳኝነት ሥርዓት ለመገንባት የሚያስችል አቅጣጫን ይጠቁማል፡፡

2. የህጉ ይዘትና መንፈስ፡- የሰበር አሠራር ህጋዊ መዋቅር አጭር ትንተና

2.1. የፌ/ጠ/ፍ/ቤት ሰ/ሰ/ች የሥልጣኑ መሠረት የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ህገ-መንግስት አንቀጽ ፹(፫)(ሀ) ሲሆን ይህ አንቀጽ "መሠረታዊ የህግ ስህተት ያለበትን ማንኛውም የመጨረሻ የፍርድ ቤት ውሳኔ በሰበር የማየት" ሥልጣን ይሰጠዋል፡፡ 'ፍርድ ቤት' የሚለው ቃል ፍቺው ፍጹም ትክክለኛነት ባለው መልኩ ስላልተቀመጠ በአዋጅ ለሚሰጥ ማብራሪያ ክፍት በር ይተዋል፡፡ ህገ መንግስቱን ተከትሎ የወጣውን የአዋጅ ቁጥር 25/88 ስንመለከት በአንቀፅ2(4) በሰፊው የሚታወቁትንና በሶስቱ እርከኖች የሚገኙትን የፌ/ጠ//ፍ/ቤት፣ የፌ/ከፍ/ቤት እና የፌ/መ/ደ/ፍ/ቤት መሆናቸውን ብቻ ጠቅሶ ያለፈ መሆኑን፣ ይህነኑ አዋጅ ለማሻሻል የወጣውና የአስገዳጅ የህግ ትርጉም ስርዓትን በግልፅ ይዞ የመጣውን አዋጅ ቁጥር 454/97 ሲታይ ፍ/ቤት በሚለው ትርጉም ላይ ያደረገው ለውጥ አልነበረም፡፡ በመሆኑም የአዋጅ ቁጥር 1234/13'ን' ታሪካዊ ዳራ ስንመለከት ሁሉን አቀፍ ወጥነትን ለማምጣት የተደረገን ጥረት እና በመጨረሻም ግቡን ሳይመታ የቀረውን ጉዞ የምናይበት ሁኖ ይገኛል፡፡፡ ቀዳሚው ህግ የነበረው አዋጅ ቁጥር ፬፻፶፬/፲፱፻፺፯ የሰበር ችሎቱ ትርጉም "በየትኛውም ደረጃ በሚገኝ የፌዴራልም ሆነ የክልል ፍርድ ቤት" አስገዳጅ እንደሚሆን ይደነግግ ነበር፡፡ ይህም አገላለጽ ምንም እንኳን በእንግሊዝኛው '' በፌዴራልና በክልል ም/ቤቶች'' የሚል ፍፁም ከአዋጁ አማርኛው ሙሉ ይዘት ወጣ ባለመልኩ የተቀመጠ ሀረግ የያዘ ቢሆንም የአማርኛው ቅጅ ተፈፃሚነት ያለው ከመሆኑ አንፃር ሲነበብ ግን ሀረጉ በቀጥታ ለመደበኛ ፍርድ ቤቶች ብቻ ያነጣጠረ ነበር ተብሎ ሊወሰድ ይችላል፡፡ አዋጅ ቁጥር ፩ሺ፪፻፴፬/፪ሺ፲፫ የበለጠ ግልጽነትን ለማምጣት ሞክሯል፡፡ በአዋጁ ፍ/ቤት ለሚለው ቃል የተሰጠው ትርጉም ቀድሞ ከነበሩት ህጎች ጋር ተመሳሳይ ቢሆንም ለ'የመጨረሻ ውሳኔ' የተሰጠው ትርጓሜ ግን እጅግ ሰፊ ሲሆን፣ በፍርድ ቤቶች፣ በህግ የዳኝነት ሥልጣን በተሰጣቸው አካላት እና በአማራጭ የክርክር መፍቻ ዘዴዎች የሚሰጡ ውሳኔዎችን እንደሚያካትት በግልጽ ተድንግጓል፡፡

2.2. ከዚህም በተጨማሪ በአዋጁ አንቀጽ ፲(፩)(ሰ) ስር የሰበር ሰሚ ችሎቱ "በህግ የመዳኘት ሥልጣን በተሰጠው አካል ወይም በሌሎች አካላት የተሰጠ የመጨረሻ ውሳኔ" ላይ የሰበር ሥልጣን እንዲኖረው ተደርጓል፡፡ ይህ ድንጋጌ በትክክልና ወሳኝ በሆነ መልኩ የዳኝነት ነክ አስተዳደራዊ አካላትን ውሳኔዎች በጠቅላይ ፍርድ ቤቱ የሰበር ስልጣን የሚታረሙ መሆኑን የሚያሳይ ነው፡፡ ሆኖም አዋጁ አንድ አስገራሚ የህግ አካሄድ ይከተላል፡፡ የአስተዳደራዊ አካላትን የመጨረሻ ውሳኔዎች በመሰረታዊ የህግ ስህተት መመዘኛዎች አግባብ በሰበር ችሎቱ ሊታረሙ እንደሚችሉ ተጠቃሹ አዋጅ ከአስቀመጠ በኋላ ችሎቱ በሚሰጠው የህግ ትርጉም ተገዳጅ የሆኑትን አካላት ሲገልፅ ግን ሳያካትታቸው ያልፋል፡፡ እንዲሁም የበላይነት ያለው የአዋጁ አማርኛ ቅጂ በአንቀጽ ፲(፪) ውስጥ እንደ ገዳቢ አንቀጽ ሆኖ ሲያገለግል ይታያል፡፡ ይህም የችሎቱን የህግ ትርጉም ሁሉን አቀፍ ተፈጻሚነትን በ'ፍርድ ቤት' ላይ ብቻ አድርጎ ይገኛል፡፡ የህግ አውጪው ምርጫ ግልጽ ነው፡፡ የዳኝነት ነክ አካላት በህጉ በተሰጣቸው አግባብ አይተው የሰጡት ውሳኔ በፌ/ጠ/ፍ/ቤት ሰበር ችሎቱ ታይቶ መሰረታዊ የህግ ስህተት ካለበት ሊሻር ቢችልም በዚሁ ሂደት ውስጥ ችሎቱ ያስቀመጠውን የህግ ትርጉም ግን እነዚህ አካላት በሌላ ጊዜ በሚያስተናግዱት ተመሳሳይ ጉዳይ ላይ ተፈፃሚ የማድረግ ወይም የመከተል ግዴታ የለባቸውም፡፡ ይህም የወጥነት ስርዓት የማያስገድደው በመሆኑ ጉዳዮች በየራሳቸው እየታዩ በተለያዩ ምክንያቶችና ድምዳሜዎች የተለያዩ ውጤቶች እንዲኖራቸው የሚያደርግ ይሆናል፡፡ ይህም በህክምናው ዓለም የበሽታውን ስር ከመፈወስ ይልቅ ምልክቶቹን ብቻ ማከም ውጤታማ አያደርግም የሚባለውን አገላለፅ እንድናስታውስ የሚያደርን ነው፡፡ በሁሉም የዳኝነት አካላት የህግ ትርጉም አስገዳጅ እንዲሆን ሳይደረግ ወጥነትና ተገማችነት ያለውን የዳኝነትና የህግ ስርዓት ማስፈን አይቻልምና፡፡ አሁን ያለው የሰበር ሰሚ ችሎት የህግ ትርጉም የአስገዳጅነት አድማስ ባለ ሁለት ደረጃ የዳኝነትና የፍትሕ ስርዓትን የሚፈጥር ነው፡፡ አንደኛው በአስገዳጅ የህግ ትርጉምና በወጥነት ፍለጋ የሚመራ ሲሆን፣ ሌላኛው ደግሞ በተቋማዊ ነጻነትና የማያቋርጥ የትርጉም መለያየት አደጋ ውስጥ የሚገኝ ነው፡፡ በመሆኑም ይህ ዥንጉርጉር አካሄድ ከዘመናዊ የዳኝነት ስርዓት ጋርም የማይጣጣም ነው፡፡

3. ህግ፣ ተግባር እና ግንዛቤ፡- በአስተዳደራዊ አካላት ውስጥ የአስገዳጅ የህግ ትርጉም አተገባበር

3.1. ከላይ የተገለፀው የህግ ማዕቀፍ በተግባር ያለውን ውስብስብ እውነታ ሙሉ በሙሉ የማያሳይ ሁኖ ይገኛል፡፡ በእኔ በፀሃፊው እስከ ፌ/ጠ/ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በነበረው የበርካታ አመታት የዳኝነት ስራ ልምድና የባለፉት አምስት አመታት የጥብቅና ስራ ልምድ፣ እንዲሁም ከአንዳንድ ቁልፍ የህግ ባለሙያዎች ጋር ፀሃፊው የነበረው ሙያዊ ውይይት መረጃ እንደሚያሳየው፣ ስርዓቱ የሚንቀሳቀሰው በግልጽ ግዴታ ላይ ተመስርቶ ሳይሆን፣ "'በአሳማኝ ሥልጣን" እና "በዳኝነት ነጻ ምርጫ" መካካል ባለው በውል ሊለይ በማይችል ቀጠና ውስጥ ነው፡፡ ቀድሞ በነበረኝ የፌ/ጠ/ፍ/ቤት ሰ/ሰ/ችሎት ሰብሳቢ ዳኝነት ሚና ጉዳዩን ስመለከተውና ቆም ብየ ሳስታውስው ጉዳዩ ከአሳሳቢ ጉዳዮች መካከል አንዱ ተደርጎ አይወሰድም ነበር፡፡ ይልቁንም አስገዳጅ የሆነ የህግ ትርጉም ያልተከተለ የዳኝነት ነክ አካላት ውሳኔ ሲያጋጥም መሰረታዊ የሆነ የህግ ስህተት እንዳለበት ተደርጎ ይወስን ነበር እንጂ የአስገዳጅ የህግ ትርጉም የአስገዳጅነት አድማስ ለየትኞቹ የዳኝነት አካላት እንደሆነ የሚለይበት አጋጣሚ አልነበረም፡፡ አሁንም ያለው አሰራር የተለይ አይደለም፡፡ ሆኖም በህጉ የተቀመጠው ገደብ ግን የሰበር ሰሚ ችሎቱ በአገሪቱ የዳኝነት ስርዓት ውስጥ ሊጫወተውና ሊኖረው ከሚገባው ሚና አንፃር ሲታይ ማናኛውንም የሰበር ሰሚ ችሎት ዳኛ ሊያሳዝን የሚችል ነው፡፡ ምክንያቱም የችሎቱ ዳኞች ከህገ መንግስት ትርጉም በመለስ በፌዴራልም ሆነ በክልል ህጎች ላይ በአዲሱ አዋጅ በተቀመጠው መመዘኛ አግባብ በማየት መሰረታዊ የህግ ስህቱን የማረም እና የህግ ትርጉም ያለበትን የመጨረሻ ዳኝነት የሚሰጡ ሁነው እያለ ከተወሰኑ አስተዳደራዊ አካላት ተመሳሳይ የትርጉም ስህተቶች ደጋግመው ሲመጡ እንደሚያዩ ይታወቃል፡፡

3.2. የእነዚህ አካላት ውሳኔዎች በሰበር ችሎት ታይተው ሊሻሩ እንደሚችሉ ህጉ የፈቀደው ከመሆኑም በተጨማሪም በተጨባጭ ያለው ሁኔታ ይህንኑ ያሳያል፡፡ ችሎቱ በህጉ በተሰጠው ስልጣን ጉዳዩን አይቶ ከሻረው ከሁለት ዓመት በኋላ ተመሳሳይ የሆነ ጉዳይ እንደገና ሲመጣ ችሎቱ ጊዜውንና ጉልበቱን ጥቅም ላይ በማዋል ተመልክቶ ቀድሞ ከሰጠው ትርጉም ጋር ተመሳሳይ ከሆነ በተመሳሳይ መንገድ የመወሰን ኃላፊቱን ይወጣል፡፡ በዚህ ሂደት የሰበር ሰሚ ችሎት ቁልፍ ሚና ሀገር አቀፍ መስፈርት ከማስቀመጥ ይልቅ ተደጋጋሚ የማስተካከያ እርምጃዎችን ወደ መውሰድ ዝቅ ይላል ማለት ነው፡፡ ይህ የሰበርን ዓላማ ራሱንም የሚንድ ነው፡፡ ይህ አመለካከት በህግ ማዕቀፉ የተፈጠረውን ስርዓታዊ ብቃት ማነስ ያሳያል፡፡ ይህም የሀገሪቱን ከፍተኛ የዳኝነት አካል ተደጋጋሚ እና አላስፈላጊ በሆነ የሥራ ዑደት ውስጥ እንዲገባ ያስገድደዋል፡፡ በፀሃፊው ልምድ የዳኝነት ነክ አካላት ዳኞች ለሰበር ችሎቱ የህግ ትርጉሞች መልካም አመለካከት አላቸው፡፡ የሰበር ችሎቱን ውሳኔዎች ሆን ብለው ችላ አይሉም፡፡ የእነዚህ አካላት ዳኞች የሰበር ችሎቱን ውሳኔዎቹን የሚመለከቱት በበተቋማዊ ተልዕኳቸውመነጽር ነው፡፡ በእነዚህ አካላት የሚሰጡ በርካታ ውሳኔዎች በእርግጥ የሰበር ውሳኔዎችን ዳኞቹ እንደሚያነቧቸው፣ የሰበር ችሎቱ ውሳኔዎች አሳማኝነት ያላቸው መሆኑን፣ ዘርፍ ለሚገኝ ፍትሐዊ እና ቀልጣፋ ውጤት ሲስማሙም እንደሚጠቅሷቸው ይመስክራሉ፡፡ ሆኖም ዳኞቹ አጠቃላይ ሥልጣን ያለን ፍርድ ቤት እንዳልሆኑ፣ የዳኞቹና የተቋሞቻቸው ዋነኛ ኃላፊነት ላቋቋሟቸው አዋጅና የፖሊሲ ዓላማዎች መሆኑን በቃል ክርክርና በማስረጃ አስማም ሂደት በሚያንፀባርቋቸው ሃሳቦች ጎልተው ሲወጡ ይታያል፡፡

3.3. አንድ አስገዳጅ የህግ ትርጉም ለአስተዳደራዊ አሰራር የማይመች ወይም ከዘርፉ ፖሊሲ ጋር የሚጋጭ ውጤት የሚፈጥር ከሆነ፣ ህጉን ላይከተሉ የሚያስችል ክፍተት ይሰጣቸዋል ማለት ነው፡፡ የእነዚህ ተቋማት ዳኞች በህግ እንደሚገዙ የሚታመን ቢሆንም የአዋጅ ቁጥር 1234/13 አንቀጽ ፲(፪) ግን የሰበር ችሎቱ የህግ ትርጉም ዳኞቹን የማስገደድ ኃይል እንደሌለው ግልጽ ያደርጋል፡፡ ይህ በምርጫ ላይ የተመሠረተ ተገዥነትን ያሳያል፤ ይህም አስገዳጅ የህግ ትርጉሞች እንደ ተዋረዳዊ ግዴታ ሳይሆን እንደ መሳሪያነት ብቻ ጥቅም ላይ እንደሚውሉ ያመለክታል፡፡ በሁለቱም መድረኮች ክርክር የሚያቀርቡ ከፍተኛ የህግ ባለሙያዎች የዚህ ክፍፍልን መዘዝ በቅርበት ይለማመዳሉ፡፡ አንዳንድ ጠበቆች እንደሚሉት "የክርክር ስትራቴጂ እንደ መድረኩ ሙሉ በሙሉ ይቀየራል፡፡ በፍርድ ቤት ፊት ሲቀረብ ዋናው ክርክር አስገዳጅ የህግ ትርጉም በተሰጠበት የሰበር ውሳኔ ላይ እንደሚመሰረት፣ በአስተዳደራዊ አካል ፊት ሲቀረብ ግን የሰበር ችሎቱ የህግ ትርጉም ያለበት ውሳኔ ከብዙ መሳሪያዎች አንዱ ብቻ እንደሆነ፣ በዚህም ምክንያት በፖሊሲ፣ በቴክኒካዊ ማስረጃ ወይም በዓለም አቀፍ ተሞክሮ ላይ ትኩረት በማድረግ ክርክር ማቅረብ ላይ ፍላጎት እንደሚያሳዩ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ሆኖም እንዲህ አይነት የክርክር አካሄድ ለደንበኞች እርግጠኝነትንና ተገማችነትን ይነሳል፤ የጉዳዩን ውጤትም በዳኝነት ነክ አካላት ዳኛው ምርጫ ላይ የተመሠረተ እንደ ዕጣ ፈንታ የማድረግ ኃይል እንዳለው ይታመናል፡፡እንዲህ አይነት ሁኔታና የጠበቆች አመለካከት የህግ የበላይነት ቁልፍ ክፍሎች በሆኑት የህግ እርግጠኝነት እና ተገማችነት ላይ ያለውን አሉታዊ ተጽዕኖ የሚያሳይ ነው፡፡

4. ወጥነት እና ቁጥጥር፡ የንጽጽራዊ የህግ ሞዴሎች

4.1. የፌ/ጠ/ፍ/ቤት ሰ/ሰ/ችሎት የህግ ትርጉም አስገዳጅነት በሁለት የዳኝነት አካላት የተከፈል ከሌሎች ሀገራት የህግ ሥርዓቶች አንጻር ሲታይ የተለየ ይመስላል፡፡ ሌሎች የህግ ሥርዓቶች በአወቃቀራቸው የተለያዩ ቢሆኑም በሁሉም የዳኝነት አካሎቻቸው ላይ የሚዘረጋ የህግ አስተምህሮ ወጥነትን ለማረጋገጥ የጋራ ቁርጠኝነት ያሳያሉ፡፡ ለምሳሌ ፈረንሳይ የሲቪል ህግ ሥርዓት ተምሳሌት እንደመሆኗ፣ በ"ኩር ደ ካሳስዮን" (Cour de cassation) የሚመሩትን የዳኝነት ፍርድ ቤቶች እና በ'ኮንሴይ ዴታ' (Administrative Supreme Court (Conseil d'Etat) (CE)) ሥር ያሉትን የአስተዳደር ፍርድ ቤቶች በጥብቅ ትለያለች፡፡ ሆኖም እያንዳንዱ ምሰሶ የራሱ የሆነ ጥብቅ ውስጣዊ ወጥነትን ይጠብቃል፡፡ አንድ የአስተዳደር አካል የ'ኮንሴይ ዴታ'ን የዳኝነት አቋም ያለ ምንም ጥያቄ የመከተል ግዴታ አለበት፡፡ ስርዓቱ ወጥነትን የሚያገኘው በአንድ የበላይ ፍርድ ቤት ሳይሆን በትይዩ በሚሄዱ የዳኝነት ተዋረዶቹ ጥብቅ ዲሲፕሊንም ጭምር ነው፡፡ የጀርመን አገር ሁኔታ ሲታይም የፌዴራል ሥርዓት ሌላ የተደራጀ የወጥነት ሞዴል ማሳያ ሁኖ ይገኛል፡፡ በጀርመን ስርዓት ውስጥ የራሳቸው የፌዴራል የበላይ ፍርድ ቤት ያላቸው ልዩ የፍርድ ቤት ሥርዓቶች (አስተዳደራዊ የሠራተኞች፣ የማኅበራዊ ዋስትና) እንዳሉ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ የፌዴራል አስተዳደር ፍርድ ቤት ለሁሉም የታችኛው የአስተዳደር ፍርድ ቤቶች እና ትሪቡናሎች የአስተዳደር ህግን ወጥ ያደርጋል፡፡ ከሁሉም በላይ እነዚህ ሁሉ ሥርዓቶች በፌዴራል ህገ-መንግስታዊ ፍርድ ቤት ሥር ሲሆኑ ይህም የህገ-መንግስታዊ መርሆዎች በሁሉም የህግ ሥርዓቱ ላይ ወጥ በሆነ መልኩ መተግበራቸውን ማረጋግጫ ነው፡፡ የህንድ አገር ልምድ ሲታይም በጣም ቀጥተኛ ለሆነው ተቃራኒ ሞዴል ማሳያ ሁኖ ይገኛል፡፡ ህንድ የኮመን ሎ ስርዓት የምትከተልና የፌዴራል ስርዓት ያላት ሀገር እንደመሆኗ መጠን የህገ-መንግስታዊ ማዕቀፏ በዳኝነት ውጤቱ በግልጽ አንድ ወጥ ነው፡፡ የህንድ ህገ-መንግስት አንቀጽ 141"በጠቅላይ ፍርድ ቤት የታወጀው ህግ በህንድ ግዛት ውስጥ ባሉ ሁሉም ፍርድ ቤቶች ላይ አስገዳጅ ይሆናል" ሲል ኃይል ቃል ባለው መልኩ በከፍተኛው የህግ ተዋረድ ላይ ባለው ሰነድ ደንግጓል፡፡ ይህ ድንጋጌ በህንድ የዳኝነት አካላት በተደጋጋሚ ሲተረጎም መደበኛ ፍርድ ቤቶችን ብቻ ሳይሆን ሁሉንም ትሪቡናሎች እና የዳኝነት ነክ ሥልጣን ያላቸውን አካላት እንደሚያካትት የሚያስገነዝብ ነው፡፡ ይህ ሞዴል ከአንድ የበላይ ፍርድ ቤት የሚመነጭ ፍጹም የዳኝነት ወጥነትን በልዩ ትሪቡናሎች ተቋማዊ ነጻነት ላይ ያስቀድማል፡፡

4.2. እነዚህ ንጽጽራዊ ምሳሌዎች እንደሚያሳዩት ምንም እንኳን መዋቅራዊ መፍትሄዎች ቢለያዩም መሠረታዊው መርሁ አንድ መሆኑን ነው፡፡ ስኬታማ የህግ ሥርዓቶች የዳኝነት ነክ አካላት ከአገሪቱ የበላይ የዳኝነት አካል አስገዳጅ የህግ ትርጉም ውጪ ሆነው እንዲንቀሳቀሱ የሚያደርግ ክፍተት በህጋቸው ውስጥ አያካትቱም፡፡ አሁን ስራ ላይ ያለው የፌ/ጠ/ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የአስገዳጅ የህግ ትርጉም ስርዓት/ሞዴል/ የፈረንሳይን ጥብቅ ሁለትዮሽነት፣ የጀርመንን የተደራጀ ልዩ ሙያዊነት፣ ወይም የህንድን አንድ ወጥ ተዋረድ ያልተከተል፤ ከመልካም ተሞክሮዎች ውጪ የወጣ ሁኖ ይታያል፡፡

5. የወጥነት መርህ መጣስ? - የንድፈ-ሀሳባዊ እና ህገ-መንግስታዊ ሂስ

5.1. የፌ/ጠ/ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የአስገዳጅ የህግ ትርጉም ስርዓት በተግባር ምሉዕ ብቃት ሊኖረው የሚችል ብቻ ሳይሆን በንድፈ-ሀሳብ እና በህገ-መንግስታዊነትም ያልጸና ነው፡፡ ከተረጋገጡ የህግ ንድፈ-ሀሳቦች አንጻር ሲለካ ጉድለቶቹ ጎልተው ይታያበታል፡፡ ከጆሴፍ ራዝ የህግ የበላይነት ጽንሰ-ሀሳብ አንጻር ሲታይ ስርዓቱ ቁልፍ መስፈርቶችን አያሟላም፡፡ በእኚህ እውቅ ምሁር አባባል መሰረት የአንድ ህግ ትርጓሜ እንደ ዳኝነት ሰጪው አካል የሚለያይበት የህግ ማዕቀፍ ግልጽ፣ ጸንቶ የቆመ ወይም ተገማች ነው ተብሎ ሊወሰድ አይችልም፡፡ ምሁሩ ግልፅነት የጎደለው፣ በየጊዜውና በየቦታው የሚለዋወጥ፤ ተገማችነት የሌለው የህግ ስርዓት ለዘፈቀደ ውሳኔዎች የተመቸ የህግ እርግጠኝነት የጎደለው ምህዳርን ይፈጥራል ሲሉ ጉዳዩን ያብራሩታል፡፡

5.2. የሮናልድ ድዎርኪን የተባሉ ምሁር ደግሞ 'አንድ የሞራል የህግ ሥርዓት ዜጎችን በተመሳሳይ መርሆች ላይ ተመስርቶ በአንድ ወጥ ድምጽ ለማነጋገር መጣር ይኖርበታል ሲሉ ይገልፃሉ፡፡ በዚህ የምሁሩ አገላለፅ በሁለት ገፅታ የተከፈለው የፌ/ጠ/ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የአስገዳጅ የህግ ትርጉም ስርዓት የአገሪቱን የዳኝነት ስርዓት በሁለት ልሳን እንዲናገር የሚያስችል መዋቅር ያላበሰ ነው፡፡ በሌላ አገላለፅ በመደበኛ ፍርድ ቤት ለቀረበ አንድ ተከራካሪ ከሰበር ችሎቱ አስገዳጅ የህግ ትርጉም በመነሳት ህጉ አንድ ግልጽ ትርጉም እንዳለው ሲነገረው በተመሳሳይ ጊዜ ደግሞ አንድ ዳኝነት ነክ አካል በተመሳሳይ ሁኔታ ላይ ላለ ሌላ ተከራካሪ የተለየ ትርጉም ሊሰጠው እንደሚችል የሚፈቅድ ነው፡፡ እንዲህ አይነት አካሄድና አሰራር ደግሞ የወጥነት መርህ ፍፁም ተቃራኒ ነው፡፡ ከሁሉም በላይ አሳሳቢው ግን ከዚህ አይነት ስርዓት የሚያስከትለው ጥልቅ ህገ-መንግስታዊ ችግር ነው፡፡

5.3. በሌሎች አገሮች ያሉት በሰበርም ሆነ በሌላ አይነት ስርዓት የመጨረሻ የዳኝነት ስልጣን ያላቸው አካላት በተፈጥሮአቸው ሊኖራቸው ከሚገባቸው ውስጥ የዳኝነት ወጥነትንና ተገማችነትን በማስፈን የህግ የበላይነትን የማረጋገጥ መሆኑ ይታመናል፡፡ የፌ/ጠ/ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የሰበር ሰበር ስልጣን እንዲኖረው በህገ መንግስቱ ታሳቢ ከተደረጉ ምክንያቶች ውስጥም የህግ ትርጉም ወጥነትና ተገማችነት በአገሪቱ ውስጥ ማስፈን መሆኑን በዚህ ረገድ የተናከወኑ ውይይቶችን የሚያሳዩ ሰንዶች አስረጅ ናቸው፡፡ ስለዚህ ሰበር ችሎቱ በህገ መንግስቱ በተሰጠው የሰበር ስልጣን እና በሌሎች አገሮች ከዳበረው አሰራር እንዲሁም የአንድ አገር የዳኝነት አካል በተፈጥሮው ሊኖረው ከሚገባው ሚና አንፃር የሚሰጠው የህግ ትርጉም አስገዳጅነቱ በማናቸውም የዳኝነት አካል መሆን ሲገባው የህግ አውጪው በቀላል አዋጅ አማካኝነት የሀገሪቱን ከፍተኛ የዳኝነት አካል ህገ-መንግስታዊ ሥልጣን መገደቡ እጅግ ሊያሳስብ የሚገባ ጉዳይ ሁኖ ይታያል፡፡ በሌላ አገላለፅ ተጠቃሹ አዋጅ የሰበር ችሎቱን አስገዳጅ የህግ ትርጉም ተፈጻሚነት በመወሰን፣ ሰበር ችሎቱ ''ህጉ ምንድን ነው'' ብሎ ለመወሰን ያለውን የመጨረሻ እና የተፈጥሯዊ ስልጣን ሚና ጥሷል፡፡ ይህም የችሎቱን የዳኝነት ስርዓትን ወጥነት የማስፈን ሚና የአስፈጻሚው ክፋይ መሆናቸው በሰፊው ለሚታመኑ ዳኝነት ነክ አካላት ነጻነት በማስገዛት፣ ስስ የሆነውን የሥልጣን ክፍፍል ሚዛን የሚያዛባ ስርዓት መዘርጋቱን የሚያስገነዝብ ነው፡፡

6. ማጠቃለያ፡ ወደ አንድ ወጥ የዳኝነት ሥርዓት

ይህ አጥር ያለውንና የተሟላ የምርምር ዘዴ ተግባራዊ ሳይደረግ በፀሃፊው የዳኝነትና የጥብቅና ልምድና ምልክታ ላይ ተመርኩዞ የተዘጋጀው ፅሁፍ የዳኝነት ነክ ሥልጣን ያላቸው አካላት ከሰበር ሰሚ ችሎት አስገዳጅ የህግ ትርጉም ስርዓት ውስጥ በግልጽ መገለላቸው ጥቃቅን የቴክኒክ ጉዳይ ሳይሆን የኢትዮጵያ የህግ ሥርዓት ትልቅ መዋቅራዊ ጉድለት መሆኑን ለማሳየት የተሞከረበት ነው፡፡ ይህ የህግ አውጪው ምርጫ ህገ-መንግስታዊ ውጥረትን፣ የንድፈ-ሀሳብ አለመጣጣምን እና የተግባር ችግርን የሚያስከትል መሆኑንም ፅሁፉ ያስገነዝባል፡፡ ይህ የሰበር አሠራር ሊያሳካቸው የተነሳላቸውን የወጥነት፣ የተገማችነት እና የህግ እርግጠኝነት ግቦችን ትርጉም አልባ የሚያደርጋቸው ናቸው፡፡ ይህንን እንቆቅልሽ ለመፍታት እና ጠንካራና ወጥ የሆነ የዳኝነትና የህግ ሥርዓት ለመገንባት ሆን ተብሎ የሚወሰድ የለውጥ እርምጃ አስፈላጊነት ሊኖር እንደሚገባ የሚጠቁም ነው፡፡

7. የመፍትሄ ሀሳቦች

7.1. የህግ ማሻሻያ፦ በጣም ቀጥተኛው መፍትሄ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአዋጅ ቁጥር ፩ሺ፪፻፴፬/፪ሺ፲፫ን አንቀጽ ፲(፪) ማሻሻል ነው፡፡ የተሻሻለው ጽሑፍ የህንድን ሞዴል በመከተል፣ የሰበር ሰሚ ችሎቱ የህግ ትርጓሜ በፌዴራልም ሆነ በክልል ደረጃ "በማንኛውም ፍርድ ቤት ወይም በህግ የዳኝነት ሥልጣን በተሰጠው አካል" ላይ አስገዳጅ እንደሚሆን መደንገግ አለበት፡፡ ይህ እርምጃ እርግጠኛ አለመሆንን እና የህግ ክፍተቱን በአንድ ጊዜ ይፈታል ተብሎ ይታመናል፡፡

7.2. የዳኝነት ህገ-መንግስታዊ ትርጓሜ (ደፋሩ መንገድ) ፦ የህግ አውጪው እርምጃ በማይወስድበት ጊዜ የሰበር ሰሚ ችሎቱ ራሱ ጉዳዩን ሊፈታ ይችላል፡፡ በአንድ ታሪካዊ ጉዳይ ላይ በህገ-መንግስቱ አንቀጽ ፹ ስር ላለው ሥልጣኑ ሰፊ ትርጓሜ ሊሰጥ ይችላል ተብሎ ይታመናል፡፡ በአንድ አካል የመጨረሻ ውሳኔ ላይ የሰበር ሥልጣን መኖር በራሱ ያን አካል በህግ ትርጓሜዎቹ የማሰር ሥልጣንን እንደሚያካትት እና ማንኛውም ይህን የሚቃረን ህግ የዳኝነት አካልን መሠረታዊ ተግባር የሚገድብ ከህገ-መንግስቱ ጋር የሚቃረን ነው በሚል ሊወስን ይችላል፡፡ ይህን ማድረግ ካልተቻል ለህገ መንግስታዊ ትርጉም ጉዳዩን ለሚመለከተው አካል መላክ እንደአማራጭ መከተል ተገቢነት ይኖረዋል ተብሎ ሊታሰብ ይችላል፡፡

7.3. የተቋማዊ ውይይት እና ቅንጅት (ተግባራዊው መንገድ)፦ ይህ እንደ ተጨማሪ እርምጃ የሚወሰድ ነው፡፡ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ከዋና ዋናዎቹ የዳኝነት ነክ አካላት አስተዳደራዊ አካላት አመራሮች ጋር መደበኛ ውይይት መጀመር አለበት፡፡ "የዳኝነት እና የአስተዳደር ዳኝነት ሰጪ አካላት ምክር ቤት" ማቋቋም የጋራ መከባበርን እና በፈቃደኝነት ላይ የተመሰረተ የህግ ትርጓሜ ውህደትን በማዳበር ወደ መደበኛ አንድ ወጥ የዳኝነት ሥርዓት የሚደረገውን ሂደትና ሽግግር ሊያቀላጥፍ እንደሚችል ይታመናል፡፡ በመጨረሻም የፌ/ጠ/ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የአስገዳጅ የህግ ትርጉም ስርዓት በመንታ መንገድ ላይ የሚገኝ ሁኖ ይታያል፡፡ ተቋሙ የህግ የበላይነትን መርሆች በሚያዳክም የተከፋፈለ ሥርዓት መቀጠል ወይም ደግሞ ችሎቱ ለሁሉም የዳኝነት አካላት ወጥነት ያለው እና ተገማች የሆነ የህግ ትርጓሜ እንዲሰጥ የሚያስችለውን ህገ-መንግስታዊ ሥልጣኑን ሙሉ በሙሉ እንዲወጣ አስፈላጊውን እርምጃ መውሰድ የግድ ይላል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ሁለተኛው መንገድ ብቻ ከዘመናዊ፣ ህገ-መንግስታዊ የፌዴራል መንግሥት ዓላማዎች፣ ግቦች እና ጥቅሞች ጋር ስምሙ ነው ተብሎ ይወሰዳል፡፡

The content of this article is intended to provide a general guide to the subject matter. Specialist advice should be sought about your specific circumstances.

[View Source]

Mondaq uses cookies on this website. By using our website you agree to our use of cookies as set out in our Privacy Policy.

Learn More